ጥቁር አሜሪካዊ ሻምበል ላይ ጥቃት የፈጸመው ፖሊስ ከሥራው ተባረረ

ፖሊስ

የፎቶው ባለመብት, Windsor Police Department

ቨርጂኒያ ውስጥ የትራፊክ መብራት ባስቆመው የአሜሪካ ሠራዊት አባል ላይ ሽጉጥ ደግኖ ዓይንን የሚያቃጥል ፈሳሽ የረጨበት የፖሊስ አባል ከሥራው ተባረረ።

ካሮን ናዛሪዮ የተባለው ወታደር ደረቱ ላይ በተገጠመው ካሜራ ፖሊሶቹ ያደረሱበትን እንግልት ቀርጾ ነበር።

ፖሊሶቹ ወታደሩን ያስቆሙት የሰሌዳ ቁጥሩ አይታይም በሚል ሲሆን ነገር ግን ቪዲዮው ላይ ጊዜያዊ የሰሌዳ ቁጥር ይታይ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ሻምበል ናዛሪዮ ጆ ጉቴሬዝ እና ዳንኤል ክሮከር በተባሉት የፖሊስ መኮንኖች ላይ ባለፈው ሳምንት ክስ መስርቶ ነበር።

ዊንድሰር የምትባለውና ቨርጂኒያ ውስጥ የምትገኝ ከተማ ባለስልጣንት ክስተቱ "የዲሲፕሊን እርምጃ እንዲወሰድ የሚያደርግና ለፖሊስ አባላቱ ተጨማሪ ስልልጠና እንዲሰጥ ምክንያት ሆኗል" ብሏል።

ጨምሮም "ድርጊቱን የፈጸመው የፖሊስ መኮንን ጆ ጉቴሬዝ ከሥራው እንዲባረር ተደርጓል" ሲል ገልጿል።

እሁድ እለት ጉዳዩን በተመለከተ የተናገሩት የቨርጂኒያ ገዢ ራልፍ ኖርዛም ክስተቱ "እንደረበሻቸውና እንዳስቆጣቸው" ገልጸዋል።

ምን ነበር የሆነው?

የአሜሪካ የጦር ሠራዊት አባል የሆነው ሻምበል ሁለት የትራፊክ ፖሊሶች ሽጉጥ በመደቀን ብሎም ዓይንን የሚያቀጥል ፈሳሽ በመርጨት (ፔፐር ስፕሬይ) ጥቃት ፈጽመውብኛል ሲል ነበር ክስ የመሰረተው።

ካሮን ናዛሪዮ የተባለው ይህ ምክትል ሻምበል የአሜሪካ ሠራዊትን የደንብ ልብስ እንደለበሰ ፖሊሶቹ ተግባሩን መፈፀማቸውን በፖሊሶች ደረት ላይ ከሚቀመጠው ካሜራ ላይ የተገኘው ተንቀሳቃሽ ምስል አመላክቷል።

ቪዲዮው እንደሚያሳየው "እውነት ለመናገር ከመኪናው ለመውረድ ፈርቻለሁ" ሲል ሁለቱን ፖሊሶች ተማፅኗል። "አዎ መፍራት አለብህ" ሲል አንደኛው ፖሊስ ሲመልስለትም ይደመጣል።

ወታደሩን ለምን እንዳስቆሙት እንዲያብራራ የተጠየቀው ፖሊስ በወቅቱ ያለ ሰሌዳ እያሽከረከረ ነበር ቢልም በቪዲዮው ላይ ግን ግዜያዊ ሰሌዳ መለጠፉ ይታያል።

ፖሊሶቹ የወታደሩን መኪና በመፈተሸ ላይ ሳሉ ሁለት እጁን በካቴና ወደ ኋላ አስረውት እንደነበር በምስሉ ላይ ይታያል።

ለምን ኃይል እንደሚጠቀሙ የሚጠይቀው ሻምበል "እየተባበርከን ስላልሆነ ነው" የሚል መልስ ከአንደኛው ፖሊስ ተሰጥቶታል። ቆይቶም ያለምንም ክስ ተለቋል።

ሻምበሉም ሕገ መንግሥታዊ መብቶቼ ተጥሰዋል ሲል በቨርጂኒያ ሁለቱን ፖሊሶች ከስሷል። በተጨማሪም ጥቃት ተፈፅሞብኛል፣ ሕገ ወጥ ፍተሻ ብሎም እስርም ተፈፅሞብኛል ሲል ፖሊሶቹን ፍርድ ቤት ገትሯቸዋል።

ከቨርጂኒያ ዊንድሶር የፖሊስ ክፍል እስከ አሁን ድረስ ምላሽ አልተገኘም። ይህንኑ ድርጊት የሚያሳየው የቪዲዮ ማስረጃ በመገናኛ ብዙሃን በሰፊው የተሰራጨ ሲሆን የሚሊዮኖች መነጋገሪያ ሆኗል።

በተጨማሪም የጆርጅ ፍሎይድን ህልፈት ተክትሎ እየተሰማ ያለው ይፋዊ የችሎት ሂደት በመላው ዓለም በመተላለፍ ላይ ባለበት ወቅት የተፈጠረ ድርጊት መሆኑም አነጋጋሪ አድርጎታል።