ፊልም፡ 7ኛው ጉማ የፊልም ሽልማትና የሥነ ሥርዓቱ ለየት ያሉት ክስተቶች

ኢትዮጵያ ውስጥ ቅዳሜ ዕለት በተካሄደው 'የጉማ' ሽልማት ላይ ከዚህ በፊት ከተካሄዱት የሽልማቱ ሥነ ሥርዓቶች የተለዩ መነጋገሪያ ጉዳዮች ተከስተዋል።

በተለይ ደግሞ ሽልማቱን ካሸነፉ የፊልም ባለሙያ ዎች መካከል አንዱ የነበረው ኢሳያስ ታደሰ በመድረኩ ላይ "እናቴ ደም ስታለቅስ፣. . . . በዚህ ሽልማት ልደሰት አልችልም" ሲል መናገሩና የታዳሚዎች አለባበስ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ባለቀለም ፊልም በሆነው "ጉማ" በተሰኘው የሚሸል ፓፓታኪስ ፊልም ስም የተሰየመው የፊልም ሥራ ሽልማት ቅዳሜ ዕለት በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል በድምቀት ተከናውኗል።

በየዓመቱ የሚካሄደው ይህ የ"ጉማ" ሽልማት ለሰባተኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን ለአንድ ዓመት በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሳይካሄድ ቆይቶ ቅዳሜ ዕለት በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል ተከናውኗል።

በዚህ ሰባተኛው የሽልማት መርሃ ግብር ላይ 45 ፊልሞች የተመዘገቡ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 15ቱ በተለያዩ 16 ዘርፎች ታጭተው እንደነበር ታውቋል።

የፊልም ባለሙያው ኢሳያስ ምን አለ?

በሰባተኛው የጉማ ሽልማት ላይ በአጭር ፊልም ዘርፍ ታጭቶ የነበረው የኢሳያስ ታደሰ ቀብድ የተሰኘ ፊልም አሸናፊ መሆን ችሏል።

ኢሳያስ አሸናፊነቱ ተገልጾ ወደ መድረኩ ከወጣ በኋላ አጭር ንግግር በትግርኛ ቋንቋ አድርጓል።

በቅድምያ "አመሰግናለሁ " ካለ በኋላ ". . .እናቴ የደም ዕምባ እያለቀሰች፣ ወንድሜ ተረሽኖ ከገደል አፋፍ ላይ እየተገፈተረ፣ ክብሯን የጠበቀች እህቴ በባለጌዎች እየተደፈረች በዚህ ሽልማት ልደሰት አልችልም።"

"የእናቴ እንባ ሲታበስ፣ አገሬ ወደ ቀደመ ክብሯ ስትመለስ እደርስበታለሁ" ሲል ነበር የተናገረው።

ወቅታዊ ጉዳዮችን እና የፖለቲካዊ አቋምም ሆነ የሃሳብ ልዩነቶችን በእንደዚህ ዓይነት መድረኮች ላይ ማንፀባረቅ አዲስ ነገር አይደለም።

እንደ ኦስካር እና ግራሚ ባሉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሽልማቶች ላይ አሸናፊዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ፕሮግራሙን የሚመሩ እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች ወሳኝ በሚባሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን አቋምና ትችታቸውን ይገልጻሉ።

በትግራይ ውስጥ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በጣም አሳሳቢ መሆኑን የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በተደጋጋሚ ይናገራሉ።

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በፌደራል መንግስቱና በህወሓት ኃይሎች መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ይገመታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድም በትግራይ ክልል ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያሳዩ ዘገባዎች መኖራቸውን ጠቅሰው በዚህ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ ሰዎች በሕግ ፊት ተጠያቁ እንደሚሆኑ መግለጻቸው ይታወሳል።

የታዳሚዎች አለባበስ

በሰባተኛው ጉማ ሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ የታደሙ ባለሙያዎች ለብሰዋቸው የነበሩት አልባሳት በተለይ በማኅበራዊው ሚዲያ ላይ ቅዳሜና እሁድ ዋነኛ መነጋገሪያ ሆነው ነበር።

በሽልማቱ ላይ ታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰዎች ታዳሚ የነበሩ ሲሆን ከመካከላቸውም ጥቂት የማይባሉት የተገኙት ለየት ባሉ ባሕላዊ እና ዘመናዊ አልባሳት ተውበው ነበር።

በተለይ አንዳንዶች የለበሷቸው ለየት ያሉ አልባሳት አድናቆትን ሲያስገኝላቸው የአንዳንዶቹ ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ከመጋራቱ በተጨማሪ ትችትም ገጥሟቸዋል።

በአገሪቱ ካለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አንጻር በሥነ ሥርዓቱ ላይ ከታደሙት እንግዶች መካከል የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አድርገው የነበሩ ሰዎች ቁጥር የሚጠበቀውን ያህል አለመሆኑ ብዙዎችን አነጋግሮ ነበር።

በጉማ አዋርድ ላይ የትኞቹ ፊልሞች ታጭተው ነበር?

በኢትዮ ፊልም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት የሚዘጋጀው ጉማ ፊልም አዋርድ "ጥሩ ብቃት ላሳዩ ፊልሞች እና አርቲስቶችን ክብርና እውቅና መስጠት" አላማው እንዳደረገ ይናገራል።

በዚህ ሰባተኛው የሽልማት መርሃ ግብር ላይ 45 ፊልሞች የተመዘገቡ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 15 በተለያዩ 16 ዘርፎች ታጭተው ነበር።

ከእነዚህ መካከል "እንሳሮ" የተሰኘው የምስግና አጥናፉ ፊልም በ13 ዘርፎች ታጭቶ ነበር።

ቁራኛዬ በ12፣ ተፈጣሪ በ10፣ ሶስተኛው ዓይን እና ወጣት በ97 በሰባት፣ ሱማሌው ቫንዳም በ6 ዘርፎች ታጭተው ነበር።

በዳይሬክቲንግ በሲኒማቶግራፊ በትወና እና በሌሎችም በአጠቃላይ 18 ዘርፎች ውድድር ተካሄዷል።

በምርጥ አጭር ፊልም ቀብድ፣ በምርጥ የፊልም ጽሑፍ እንዲሁም በምርጥ ፊልም ቁራኛዬ አሸናፊ ሲሆን በምርጥ ሲኒማቶግራፊ እንዲሁም ኤዲቲንግ ደግሞ እንሳሮ ፊልም ተሸላሚ ሆኗል።

በምርጥ ሴት ተዋናይ ዘሪቱ ከበደ በወጣት በ97 ፊልም፣ ምርጥ ዋና ወንድ ተዋናይ ደግሞ ሄኖክ አሸናፊ ሱማሌው ቫንዳም ሄላይ ባሳዩት የትወና ብቃት ተሸላሚ መሆናቸው ታውቋል።

ከዚህም በተጨማሪ በዚህ የሽልማት ዘርፍ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ የሆኑት አንጋፋው ፀሐፌ ተውኔት ገጣሚና የዜማ ደራሲ የፊልም ተዋናይ ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) ነበሩ።

ይህ ጉማ የተሰኘው ሽልማት መጠሪያውን ያገኘው ከአምሳ በፊት በሚሼል ፓፓታኪስ ከተሠራው "ጉማ" ፊልም ነው።