ኮሮናቫይረስ፡ በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት መስጠት ተጀመረ

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ የኮቪድ -19 ክትባት ሲከተቡ

የፎቶው ባለመብት, SOMALI COMMUNICATION

የምስሉ መግለጫ, የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ክትባቱን ወስደዋል

በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የኮቪድ-19 ክትባት መሰጠት የተጀመረ ሲሆን፤ በዚህም የክትባት መርሃ ግብር ጅማሬ ላይ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ኃላፊዎች ተከትበዋል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በትግራይ ክልል መቀለ ከተማ ተገኝተው ክትባቱን በመውሰድ መርሃ ግብሩን አስጀምረዋል።

"በመላ አገሪቷ ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ የሆኑ የጤና ባለሙያዎችና ሰራተኞች፣ በእድሜ የገፉና ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች በመጀመሪያ ዙር ክትባቱን በቀዳሚነት ያገኛሉ" ብለዋል ሚኒስትሯ።

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ክትባት መሰጠት የተጀመረበት የዛሬው ዕለት፤ ወረርሽኙ በአገሪቱ ውስጥ መገኘቱ ይፋ በተደረገበት ልክ በአንደኛ ዓመቱ ነው።

ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያገለግለውን 2.2 ሚሊየን ብልቃጥ ክትባት የተረከበችው ባለፈው ሳምንት ነበር።

ክትባቱ አስትራዜኔካ ሠራሽ ሲሆን ክትባቱ ኮቫክስ ከተሰኘው ዓለም አቀፍ የክትባት አቅርቦት ጥምረት የተገኘ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ ማስታወቁ ይታወሳል።

ይህም በተለያዩ ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች ተከፋፍሎ ነው ዛሬ ቅድሚያ ለተሰጣቸው ሰዎች መሰጠት የተጀመረው።

በዚህም በአዲስ አበባ፣ አማራ፣ ሐረሪ፣ ሶማሌ፣ ኦሮሚያ እና ሌሎች ክልሎች የክትባቱን መርሃ ግብር በይፋ ተጀምሯል።

ወታደራዊ ግጭት በተከሰተበት ትግራይ ክልልም፤ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በመቀለ በመገኘት የክትባቱን መርሃ ግብር አስጀምረዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ፣ የክልሉ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ሙሉ ነጋና ሌሎች ባለሥልጣናት ክትባቱን ወስደዋል።

ዶ/ር ሊያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የክትባት ውስንነት መኖሩን በመግለፅ፤ ሕብረተሰቡ ክትባት ተጀመሯል ብሎ መዘናጋት እንደሌለበት አሳስበዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የክትባት መርሃ ግብርም፤ የከተማዋ የጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ፤ ስለ ክትባቱ የሚናፈሰው ወሬ ከእውነት የራቀ መሆኑን በመግለፅ ለማሳያነት ራሳቸው መከተባቸው ተነግሯል።

በአማራ ክልልም በባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው የፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልም ውስጥ ክትባቱ ዛሬ መሰጠት ተጀምሯል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ፣ የጤና ቢሮ ኃላፊው ዶክተር መልካሙ አብቴ እና ሌሎች አመራሮች እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች ክትባቱን ወስደዋል።

ክልሉ በአገር አቀፍ በተሰጠው ኮታ መሰረትም 108 ሺህ ብልቃጥ ክትባት ማግኘቱን የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ገልጿል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድም ክትባቱን በመውሰድ የክትባት ዘመቻውን በክልሉ አስጀምረዋል።

አቶ ሙስጠፌ ክልሉ 108 ሺህ ብልቃጥ ክትባት ማግኘቱን ገልፀው፤ "ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ ሕብረተሰብ ክፍሎች በአፋጣኝ ክትባቱን እንዲያገኙ እናደርጋለን" ማለታቸው ተዘግቧል።

ክትባቱ ቅድሚያ ለጤና ባለሙያዎች የሚሰጥ ሲሆን በመቀጠልም ተጓዳኝ ህመም ላለባቸውና እድሜያቸው ለገፋ ሰዎች ይሰጣል ተብሏል።

በኢትዮጵያ የቫይረሱ ሥርጭት እየጨመረ ሲሆን በቫይረሱ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም እያሻቀበ ነው።

የቫይረሱ መሰራጨት አቅም ጨምሮ በ12.80 በመቶ በኮቪድ የመያዝ ምጣኔ መድረሱን የሕብረተሰብ ጤና ተቋም አስታውቋል።

የኮሮናቫይረስ ታማሚ የተሸፈነ አስክሬን

የፎቶው ባለመብት, EPHI

በትናንትናው ዕለትም እስካሁን ከፍተኛ የተባለው የሞት ቁጥር መመዝገቡን ተቋሙ አስታውቋል።

በትናንትናው ዕለት 27 ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን ይህ የተረጋገጠው ከአስክሬን በተወሰደ ናሙና ላይ በተደረገ ምርመራ ነው ተብሏል።

ወረርሽኙ ከጀመረ አንስቶ 2 ሺህ 510 ሰዎች በቫይረሱ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ወደ ፅኑ ሕሙማን ክፍል የሚገቡ ታማሚዎች ቁጥርም እየጨመረ መሆኑን የገለፀው ተቋሙ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቧል።

በኢትዮጵያ ወረርሽኙ ከተከሰተ አንስቶ 172 ሺህ 571 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 2 ሺህ 510 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።