የኮቪድ-19 ክትባት አዲስ አበባ ገባ

የፎቶው ባለመብት, @ChristianRogg
ዛሬ ንጋት ላይ 2.2 ሚሊዮን የኮቪድ-19 ክትባት አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ደረሰ።
ኢትዮጵያ የገባው የኮቪድ-19 ክትባት አስትራዜኔካ ሠራሽ ሲሆን ክትባቱ ኮቫክስ ከተሰኘው ዓለም አቀፍ ጥምረት የተገኘ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ አስታውቋል።
በኮቫክስ አማካኝነት ክትባቱ ኢትዮጵያ መግባቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የክትባት ስርጭቱን እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ ለሚደረገው ጥረት ማሳያ ነው ብሏል የዓለም ጤና ድርጅት በኢትዮጵያ።
የጤና ሚኒስቴር የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚውለው የመጀመሪያ ዙር ክትባት ዛሬ እንደሚገባ አስታውቆ ነበር።
ክትባቱ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የጤና ሠራተኞችን ጨምሮ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመለየት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውም ተገልጿል።
ከዚህ ቀደም የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ለክትባቱ በዋናነት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዜጎች ተጋላጭ ይሆናሉ ተብለው የተለዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እንደሆኑ አስታውቀዋል።
በዚህ መሰረት የጤና ባለሙያዎች፣ የማህበራዊ ጤና ሠራተኞች፣ የህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አካላት ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ያሉ ሲሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው ግብረ ሀይልም የተሳለጠ የክትባት አሰጣጥና ቁጥጥር እንዲኖር ያደርጋል ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ኮቫክስ ምንድነው?
ኮቫክስ የኮቪድ-19 ክትባት ለደሃ አገራት እንዲደርስ የተመሰረተ ዓለም አቀፍ ጥምረት ነው። የበለጸጉት አገራት ለኮቫክስ ኢኒሺዬቲቭ የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።
ለምሳሌ ዩናይትድ ኪንገደም በዩኬኤይድ በኩል ለኮቫክስ የ760 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን በኢትዮጵያ የዩኬኤይድ ተወካይ ክርስቲያን ሮግ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍራዋል።
በኮቫክስ አማካኝነት በአንድ ዓመት ብቻ በ190 አገራት ሁለት ቢሊዮን ክትባቶችን ለማሠራጨት ታልሟል።
በተለይ ደግሞ 92 ደሃ የሚባሉ አገራት ከሌሎች 98 አቅም ካላቸው አገራት እኩል ክትባቱን እንዲቀበሉ ይደረጋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሃገራት የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚዎች ናቸው።
ይህም ማለት አፍሪካ በዚህ ኢኒሼቲቭ በኩል፣ 220 ሚሊዮን ክትባቶችን ታገኛለች።
ፕሮግራሙ እስካሁን ድረስ ለክትባት የሚሆን 6 በሊየን ዶላር ማሳበሳብ ችሏል። ቢሆንም ተጨማሪ 2 ቢሊየን ዶላር ያስፈልጋል እየተባለ ነው።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ኢትዮጵያና መሰል ሀገራት ከኮቫክስ የክትባት ትብብር ተቋም ጋር በመሆን እስከ ፈረንጆቹ 2021 መጨረሻ 20 በመቶ የሚሆነውን ህዝባቸውን ለመከተብ እየሰሠሩ ነው ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ምንም እንኳን በአፍሪካ በቫይረሱ የተያዙ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በንፅፅር ዝቅተኛ ቢሆንም በአንዳንድ አገራት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በድጋሚ እየጨመረ ነው።
በኢትዮጵያም ወረርሽኙ ከተከሰተባት ዕለት ጀምሮ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ጭማሪ እያሳየ ሲሆን እስካሁንም ባለው አሃዝ 165 ሺህ 29 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፤ ከነዚህም ውስጥ 137 ሺህ 785 ሲያገግሙ 2 ሺህ 420 ሕይወታቸው አልፏል።













