በዓለማችን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የመንትዮች ቁጥር ጨምሯል

መንትዮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዓለማችን ከዚህ በፊት አይታው በማታውቀው መጠን በመንትዮች እየተሞላች እንደሆነ አጥኚዎች አረጋገጡ።

በየዓመቱ 1.6 ሚሊዮን መንታ ልጆች ይወለዳሉ። ይህ ማለት ከ42 ሕፃናት መካከል መንታዎች አሉ ማለት ነው።

ዘግይቶ ማርገዝና አንዳንድ የሕክምና መላዎች ከ1980ዎቹ በኋላ የመንታ ልጆች የውልደት መጠንን በሦስት እጥፍ እንዲያድግ አድርጎታል።

ነገር ግን የመንታ ልጆች ውልደት መጠን ከዚህ በኋላ እንደሚቀንስ ይገመታል።

ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት አንድ ልጅ ብቻ ወልዶ ማሳደግ አዲሱ የሕይወት ዘይቤ እየሆነ መምጣቱ ነው።

ሂዩማን ሪፕሮዳክሽንስ የተሰኘው ጋዜጣ ላይ የወጣ ዘገባ እንደሚያሳየው ባለፉት 30 ዓመታት የመንታ ልጆች ዕድገት እስያ ውስጥ 32 በመቶ ሲጨምር ሰሜን አሜሪካ በ71 በመቶ ተመንድጓል።

አጥኚዎቹ በፈረንጆቹ ከ2010-15 ባለው ጊዜ ከ165 አገራት የሰበሰቡትን ጥናት ከ1980-85 ካለው ጋር አነጻጽውታል።

በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ከአንድ ሺህ አዲስ የሚወለዱ ሕፃናት የመንታዎች ቁጥር ጨምሯል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ከአንድ ሺህ ሕፃናት መካከል 12 መንታዎች ይወለዳሉ።

በአፍሪካ የሚወለዱ የመንታ ልጆች መጠን በፊትም ባለፉት 30 ዓመታት ከፍተኛ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የሕዝብ ብዛት ነው ይላሉ አጥኚዎች።

አፍሪካና እስያ በዓለማችን ካሉ መንታዎች 80 በመቶውን በመያዝ ቀዳሚዎቹ አህጉራት ናቸው።

የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ክርስቲያን ሞንደን ለዚህ አንድ ምክንያት አሉ ይላሉ።

"በአፍሪካ የመንታ ልጆች ቁጥር እየጨመረ ያለበት አንዱ ምክንያት ከሁለት የተለያዩ እንቁላሎች መወለዳቸው ነው።"

"ይህ የሚሆንበት አንደኛው ምክንያት በአፍሪካ ሕዝብና በሌላው ሕዝብ መካከል ያለው የዘረ-መል (ጄኔቲክ) ልዩነት ሊሆን ይችላል።"

የመንታ ልጆች ውልደት መጠን በአውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካና ኦሺኒክ አገራትም ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ ነው።

ለዚህ እንደምክንያት የሚቆጠረው ከ1970ዎቹ በኋላ እየተለመደ የመጡት ሳይንሳዊ መላዎችን ተጠቅሞ መንታ ልጆች መውለድ መለመዱ ነው።

ሴቶች ዘግይተው ልጅ መውለዳቸው፣ የወሊድ መቆጣጠሪያዎች መበራከት፣ እንዲሁም የውልደት መጠን መቀነስ ለመንታ ልጆች ውልደት መጠን መጨመር አስተዋፅዖ እያበረከቱ ነው።

ነገር ግን አሁኑ ትኩረቱ አንድ ልጅ ብቻ ወደማሳደግ እየዞረ መጥቷል፤ ይህ ተመራጭ ነው ይላሉ ፕሮፌሰር ሞንደን።

ፕሮፌሰር አንድ ልጅ ብቻ ለመውለድ መሞከር መልካም ነው ብለው የሚያስቡት መንታ ልጆችን የሚያረግዙ እናቶች በእርግዝና ወቅት፣ በወሊድ ጊዜና እንዲሁም ከወሊድ በኋላ ብዙ ችግር እንደሚያጋጥማቸው ጥናቶች ስለሚጠቁሙ ነው።

ከወሊድ በኋላም ቢሆን በተለይ ደግሞ በዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት መንታ ልጆችን ማሳደግ ቀላል አይደለም።

ለምሳሌ ከሰሃራ በታች የአፍሪካ ክፍል ውስጥ በርካታ መንታ ልጆች በመጀመሪያው ዓመት አብረዋቸው የተወደለዱ ልጆችን ያጣሉ።

ወደፊት ለሚታየው የመንታ ልጆች ውልደት መጠን ቻይናና ሕንድ የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚችል ይታመናል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ብዙዎች መንታ የሆኑባት የናይጄሪያዋ ከተማ