ህንዳዊቷ በ73 ዓመታቸው መንታ ተገላገሉ

በሕንድ ደቡባዊ ግዛት አንድህራ ፕራደሽ የ73 ዓመቷ አዛውንት የመንታ ሴት ልጆች እናት ሆነዋል። አዛውንቷ ባሳለፍነው ሐሙስ በሐኪሞች እገዛ የሴትን እንቁላልና የወንድ ዘር ፈሳሽ (ስፐርም) በቤተ ሙከራ በማዋሃድ [IVF treatment] መንትዮች ጸንሰው ዐይናቸውን በዐይናቸው ማየት ችለዋል።
የ73 ዓመቷ ማንጋያማያ ማርቲ እንዳሉት፤ እሳቸውና የ82 ዓመቱ ባለቤታቸው ልጅ መውለድ ቢፈልጉም እስካሁን ድረስ ሳይሳካላቸው ቆይቶ ነበር።
ማንጋያማያ ሁለቱን መንታ ሴት ልጆች የወለዷቸው በቀዶ ሕክምና ነው።
ሀኪማቸው የነበሩት ዶ/ር ኡማ ሳንካራም፤ እኝህ እናት ከነልጆቻቸው በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ አረጋግጠዋል።
ልጆቹ ከተወለዱ ከሰዓታት በኋላ ቢቢሲ ያነጋገራቸው አባት ሲታራማ ራጃሮ በበኩላቸው " በጣም ተደስተናል" ብለዋል። ይሁን እንጂ ይህንን በተናገሩ ማግስት ድንገተኛ ስትሮክ ስላጋጠማቸው በሆስፒታል ውስጥ የሕክምና ክትትል እያደረጉ ይገኛሉ።
እድሜያቸው በመግፋቱ ምክንያት በባለቤታቸውና በእሳቸው ላይ አንድ ነገር ቢፈጠር ልጆቹን ማን ሊያሳድጋቸው ይችላል? ተብለው የተጠየቁት የ82 ዓመቱ አዛውንት ሮጀር፤ "በእጃችን ላይ ምንም ነገር የለም፤ መሆን ያለበት ይሆናል፤ ሁሉም ነገር በፈጣሪ እጅ ነው ያለው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በመንደራቸው ልጅ ባለመውለዳቸው መገለል ይደርስባቸው እንደነበር የሚናገሩት ጥንዶቹ፤ ልጆች መውለድ ለነሱ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያስረዳሉ። እናት ማንጋያማያ፤ "ልጅ አልባዋ ሴት እያሉ ይጠሩኝ ነበር" ሲሉ ይደርስባቸው የነበረውን የሥነ ልቦና ጫና ያስታውሳሉ።
"ብዙ ጊዜ ሞክረናል፤ በርካታ የሕክምና ተቋማትንም ጎብኝተናል" በማለት አሁን ግን በሕይወት ዘመናቸው ደስታን የተጎናፀፉበት ጊዜ እንደሆነ ይገልፃሉ።
ከሦስት ዓመታት በፊትም እዚያው ሕንድ ውስጥ በ70ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ዳለጂንደር ካዩር የተባሉ አዛውንት ወንድ ልጅ መውለዳቸው ይታወሳል።















