የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ያቋረጠው ኮሪያዊ ቢሊየነር ሆነ

የደቡብ ኮሪያው ቢሊዮነር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የደቡብ ኮሪያው የኢ-ኮሜርስ ግዙፍ ድርጅት ኩፓንግ የገበያ ድርሻውን በኒው ዮርክ የአክሲዮን ላይ አስመዘገበ።

የድርጅቱ መሥራች ደቡብ ኮሪያዊው ቦም ኪም ነው።

ቦም ኪም የሃርቫር ቢዝነስ ስኩል ተማሪ የነበረና አቋርጦ የወጣ ነው።

በኒው ዮርክ የአክሲዮን ገበያ ላይ የዚህ ሰው የገበያ ድርሻ በአሁኑ ወቅት ከ8.6 ቢሊዮን ዶላር ሆኗል። ሰውዬውም የቢሊየርነት መዝገብ ላይ ሰፍሯል።

ኩባንያው አሜሪካ ውስጥ ከተመዘገቡ የእስያ ኩባንያዎች በፈረንጆቹ 2014 ከተመዘገበው አሊባባ በመቀጠል ትልቁ ነው ተብሏል።

ምንም እንኳ ድርጅቱ አሁን ላይ ኪሳራውን እያካካሰ ቢሆንም ባለፈው ዓመት በተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የበይ መረብ ገበያ መድራቱ ትርፋማ አድርጎታል።

ድርጅቱ ወደ አሜሪካ የአክሲዮን ገበያ ሲዘልቅ የነበረው 41 በመቶ የገበያ ድርሻ ኡበር ከተሰኘው ድርጅት በመቀጠል ትልቁ እንዲሆን አድርጎታል።

ኩፓንግ የደቡብ ኮሪያው አማዞን ነው የሚል ስያሜም የሰጡት አልጠፉም።

ኩፓንግ በበይነ-መረብ ዕቃዎችን በችርቻሮ ይሸጣል። ኩባንያው ከጃፓኑ አህጉራዊ ባንክ ሶፍትባንክ ነው ብድር አግኝቶ ወደ ሥራ የገባው።

የኩፓንግ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ የሆነው ኪም የተወለደው የደቡብ ኮሪያ ዋና ከተማ ሴውል ነው።

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ ነው ወደ አሜሪካ መጥቶ የዩናይትድ ስቴትስ ዜግነት ያገኘው።

በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እየተከታተለ የነበረው ኪም በፈረንጆቹ 2010 ትምህርቱን አቋርጦ ወደ ሃገሩ በመመለስ ድርጅቱን አቋቋመ።

ድርጅቱ አቅሙን በማስፋፋት በአሁኑ ወቅት ከ70 በመቶ በላይ ደቡብ ኮሪያዊያንን መድረስ ችሏል።

ኩባንያው ከችርቻሮ ንግድ አልፎ አሁን ምግብ ወደማድረስና የመዝናኛ ፕሮግራሞችን ወደ ማሰራጨት እየሄደ ነው።

ምንም እንኳ ኩባንያው ስኬታማነቱና ታዋቂነቱ ከጊዜ ጊዜ እየሰመረ ቢመጣም ሠራተኞች ከአቅም በላይ እየሠሩ ነው የሚል ቅሬታ ይነሳበታል።

ደቡብ ኮሪያዊ ኩባንያ ለመጋዘን ሠራተኞቹና ከ15 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ቋሚ ዕቃ አድራሽ ሠራተኞቹ 90 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ አክሲዮን ይሰጣል ተብሏል።