የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ "ተገፍቶ መውጣቱን" ገለፀ

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከሦስት ወራት በኋላ ይካሄዳል ከተባለው ምርጫ ከፍላጎቱ ውጪ በደረሱበት ጫናዎች ለመውጣት መገደዱን አስታወቀ።

የፓርቲው ፀሐፊ የሆኑት አቶ ጥሩነህ ገምታ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የኦሮሞ ፌደራሊስ ኮንግረስ ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ "ተገፍቶ ለመውጣት ተገድዷል" ብለዋል።

ኦፌኮ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሲያወጣቸው በነበሩ መግለጫዎች የታሰሩ አመራሮቹ እንዲፈቱ፣ በኦሮሚያ የተለያዩ ስፍራዎች የተዘጉ ቢሮዎቻቸው እንዲከፈቱ፣ እንዲሁም ታማኝነት ያለው ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል አገራዊ ምክክር እንዲደረግ ጥሪ ሲያቀርብ ነበር።

ኦፌኮ ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ በተካሄዱ አገራዊ ምርጫዎች ላይ ተሳታፊ የነበረ ሲሆን ከምርጫ ውድድር እራሱን ሲያገል ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል።

አቶ ጥሩነህ ገምታ ባለፈው ሳምንት ከምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች ጋር ፖለቲካ ፓርቲዎች የዕጩ ምዝገባን በተመለከተ በተደረገ ውይይት ላይ መሳተፋቸውን አስታውሰው፤ ኦፌኮ ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ካልተሟሉ ዕጩ እያስመዘገበ እንዳልሆነ እና ማስመዝገብም እንደማይችል፣ ስለዚህም ምርጫው ላይ መሳተፍ እንደማይችል ለምርጫ ቦርድ አስታውቋል ብለዋል።

በተጨማሪም የፖለቲካ ምኅዳር መጥበብ እና ምርጫው ላይ አገራዊ መግባባት አለመኖር ምርጫው ፍትሃዊ እና ተዓማኒነት እንዲኖረው እንደማያደርግ በስበሰባው ላይ መናገራቸው አስታወሰዋል።

ሆኖም ግን ፓርቲያቸው ላነሳው ሃሳብም ሆነ ላቀረባቸው ጥያቄዎች ምንም ምላሽ አለማግኘታቸውን አቶ ጥሩነህ ተናግረዋል።

በመሆኑም እነዚህ ጥያቄዎች ባልተሟሉበት ሁኔታ ፓርቲው በምርጫው ላይ ለመሳተፍ እንደማይችል አቶ ጥሩነህ ገምታ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እስካሁን ድረስ ቢሮዎቻቸው በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች ተዘግተው እንዳሉ የሚናገሩት አቶ ጥሩነህ፣ ከዋናው የፓርቲው ጽህፈት ቤት ምርጫውን እንዲያስፈጽሙ ከተመደቡ አምስት ሰዎች አራቱ እስር ቤት መሆናቸውን ተናግረዋል።

ስለዚህም "አፌን ሞልቼ መናገር የምችለው ከዚህ ምርጫ የወጣነው ተገፍተን እንደሆነ ሕዝባችንም ሆነ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ሊያውቅልን እንደሚገባ ነው።"

እስር ቤት ካሉ የኢፌኮ አመራሮች መካከል የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ፣ የፓርቲው ዋና ፀሐፊ አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ እንዲሁም ባለፈው ዓመት ፓርቲውን የተቀላቀሉት አቶ ጃዋር መሐመድን እና ሐምዛ አዳነ (ቦረና) ይገኙበታል።

"አንድ ፓርቲ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ቢያንስ ነጻ ሆኖ መንቀሳቀስ መቻል አለበት። እኛ ግን አሁንም አባላቶቻችን፣ በወረዳና በዞን ደረጃ ያሉ አመራሮች፣ እጩ ተወዳዳሪ እና ታዛቢ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎች እስር ቤት ነው ያሉት። ስለዚህ እንሳተፍ እንኳ ብንል መሳተፍ አንችልም፤ ከምርጫው የመውጣት ውሳኔ ላይ የደረሰነው ተገደን ነው" ብለዋል።

እነዚህ የምናነሳቸው ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ስንጠይቅ የቆየን ቢሆንም ባለፈው ሳምንት ግን የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ካልተመለሱ ምርጫው ላይ ላለመሳተፍ ወስኗል ብለዋል።

ከኦፌኮ በተጨማሪ በኦሮሚያ ካሉ የተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የአመራሮቹ መታሰር እና የቢሮዎች መዘጋትን በማንሳት ምርጫው ላይ ለመሳተፍ እንደሚቸገር ከዚህ በፊት ለቢቢሲ መናገሩ ይታወሳል።

በምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የዕጩዎች ምዝገባ ዛሬ የሚጠናቀቅ ሲሆን፤ ኦፌኮ እስከ ትናነትናው ዕለት ድረስ ምንም ዓይነት ዕጩ እንዳላስመዘገበ ለቢቢሲ አረጋግጧል።

አቶ ጥሩነህም የዕጩዎች ምዝገባ የሚጠናቀቅ መሆኑን ጠቅሰው ያነሷቸው ጥያቄዎች፤ የፓርቲ አመራሮቻቸው መፈታትን ጨምሮ ምላሸ የሚያገኙ ከሆነ እና የዕጩ ምዝገባ ጊዜ የሚራዘም ከሆነ ድርጅቱ አሁንም በምርጫው ውስጥ ለመቆየት ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።

አቶ ጥሩነህ ከዚህ ቀደም የኦነግም ሆነ የኦፌኮ አመራሮች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር ተገናኝተው በጉዳዩ ላይ እንደተወያዩ ተናግረው ከዚህ ውይይት በኋላ ግን ምንም ዓይነት ለውጥ አለማየታቸውን ገልጸዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ከምርጫ ቦርድም ሆነ ከመንግሥት በኩል አስካሁን የተባለ ነገር የለም።

በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሱና ዋነኛ ከሚባሉት የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል አንዱ ዮነው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ፤ በአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ይመራ በነበረው የኦሮሞ ፌደራሊስት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) እና በፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በሚመራው የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦሕኮ) መካከል በሐምሌ 2004 ዓ.ም በተደረገ ውህደት የተመሰረተ ድርጅት ነው።