መቀለ ውስጥ ታስሮ የነበረው የቢቢሲ ዘጋቢ ግርማይ ገብሩ ተለቀቀ

በኢትዮጵያ ሠራዊት መቀለ ውሰጥ በቁጥጥር ሥር ውሎ የቆየው የቢቢሲ ሪፖርተር ግርማይ ገብሩ ከእስር ተለቀቀ።
ጋዜጠኛ ግርማይ ዛሬ ረፋድ ላይ ከእስር የተለቀቀው ለሁለት ቀናት በእስር ከቆየ በኋላ ምንም አይነት ክስ ሳይመሰረትበት ነው።
ቢቢሲም ጋዜጠኛው በምን ምክያት እንደታሰረ መረጃ አላገኘም።
ግርማይ ከተያዘ በኋላ መጀመሪያ ላይ በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ የቆ ሲሆን በኋላ ላይ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተዘዋውሮ ነበር።
ግጭት በተካሄደበት የሰሜናዊ ኢትዮጵያዋ የትግራይ ክልል የቢቢሲ ትግርኛ ቋንቋ ዘጋቢ የሆነው ግርማይ ገብሩ በኢትዮጵያ ወታደሮች መታሰሩን ተከትሎ ቢቢሲ ስጋቱን ግልጾ ነበር።
የቢቢሲ ቃል አቀባይ እስሩን በተመለከተ "ስጋታችንን ለኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ገልጸን ምላሻቸውን እየተጠባበቅን ነው" ብለው ነበር።
ትግራይ ውስጥ ከግርማይ በተጨማሪ ታስረው ነበሩ የኤኤፍፒ ዜና ወኪልና የፋይናንሻል ታይምስ ዘጋቢና አስተርጓሚዎችም ከእስር መለቀቃቸው ተገልጿል።
ለቢቢሲ የትግርኛ ቋንቋ አገልግሎት የሚሰራው ግርማይ ገብሩ ሰኞ የካቲት 22 የተያዘው በክልሉ ዋና ከተማ መቀለ ውስጥ በሚገኝ ካፍቴሪያ ውስጥ ከሌሎች አራት ሰዎች ጋር ነበር።
የዓይን እማኞች ለቢቢሲ እንደተናገሩት አምሰቱ ሰዎች የተያዙት ወታደራዊ የደንብ ልብስ በለበሱ ግለሰቦች ሲሆን፤ በሁለት የወታደር ተሽከርካሪዎች በታጀበ መኪና መወሰዳቸውን ገልጸው ነበር።
ግርማይን ጨምሮ አምሰት ሰዎች ለምን ተይዘው እንደተወሰዱ ግልጽ አይደለም። ቢቢሲ ባገኘው መረጃ መሰረት ሪፖርተሩ መቀለ ውስጥ ወደሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ እንዲቆይ ተደርጓል።
ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ወደ ትግራይ ለወራት እንዳይገቡ ከተከለከለ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ አገር ጋዜጠኞች ወደ ትግራይ ገብተው እንዲዘግቡ ባለፈው ሳምንት መፍቀዱ ይታወሳል።
የቢቢሲው ዘጋቢ ታስሮ የነበረው ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ (ኤኤፍፒ) እና ለፋይናንሻል ታይምስ የሚያግዙ ባለሙያዎች (ፊክሰር) መታሰራቸው ከተነገረ ከቀናት በኋላ ነው።
ህወሓትን ለማስወገድ በተወሰደው ወታደራዊ እርምጃ የፌደራል መንግሥቱ ኃይሎች የትግራይ ክልልን መቆጣጠራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ካስታወቁ በኋላ ካለፈው ኅዳር ጀምሮ ክልሉ በወታደራዊ ዕዝ ስር ይገኛል።
ወታደራዊ ግጭቱ የተባባሰው የህወሓት ኃይሎች ትግራይ ውስጥ በሚገኘው የሠሜን ዕዝ ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ ነበር።
በውጊያው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ለመፈናቀል ተዳርገዋል፤ በተጨማሪም በክልሉ ተፈጽመዋል የተባሉ ግድያዎችና የሰብአዊ ቀውስ ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ ነው።













