ሕንዳዊው ለጥል ባዘጋጀው የገዛ አውራ ዶሮው ተገደለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሕንድ ለአውራ ዶሮዎች ጥል በዝግጅት ላይ የነበረው ዶሮ ባለቤቱን ገደለ።
ሕንዳዊው በገዛ አውራዶሮው የተገደለው የአውራ ዶሮው እግር ላይ ታስሮ በነበረው ስለት ከተቆረጠ በኋላ መሆኑን የሕንድ ፖሊስ አስታውቋል።
የአውራ ዶሮዎች ጥል በሕንድ የተከለከለ ቢሆንም በተለይም በገጠራማ የሕንድ ግዛቶች በርካቶች ድርጊቱን እንደየመዝናኛ ትርዒት ይጠቀሙበታል።
በአውራ ዶሮዎች ጥል ውርርድ ማድረግም በስፋት የተለመደ ነው።
ፖሊስ እንዳለው ሟቹ ግለሰብ እግሩ ላይ ስለት የታሰረ አውራ ዶሮውን ለጥል እያዘጋጀ ሳለ፤ አውራ ዶሮ ከባለቤቱ እጅ ለማምለጥ ሲሞክር ግለሰቡ ታፋው ላይ በስለቱ ከተቆረጠ በኋላ ብዙ ደም ፈሶት ሕይወቱ አልፏል።
ፖሊስ በስም ያልጠቀሰው ግለሰብ ዶሮው እግር ላይ ታስሮ በነበረው 7 ሴ.ሜ ርዝማኔ ባለው ቢላዋ ጉዳቱ ካጋጠመው በኋላ ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም ብዙ የደም መፍሰስ ስላጋጠመው ሕይወቱን ማትረፍ አልተቻለም ብሏል።
በሳምንቱ መጨረሻ ላይ አውራዶሮዎችን በማደባደብ ሕገ-ወጥ ተግባር ተሳትፈዋል ያላቸውን 15 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየሰራ መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል።
በስነ-ስርዓቱ የተሳተፉ ሰዎች በሰው ሕይወት ማጥፋት፣ በሕገ-ወጥ ውርርድ እና የአውራዶሮ ጥል ክስ ይመሰረትባቸዋል ሲል ኤኤፍፒ ዘግቧል።
በሕንድ በተመሳሳይ ሁኔታ በአውራ ዶሮ ምክንያት የሰው ሕይወት ሲጠፋ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
ከአንድ ዓመት በፊት አንድህራ ፕራዴሽ የተባለ ግለሰብ እግሩ ላይ ስለት በተገጠመልት የገዛ አውራዶሮ አንገቱንተቆርጦ ሕይወቱ አልፏል።
ይህ አድጋም ያጋጠመው በሕገ-ወጥ የአውራ ዶሮች ጥል ትርዒት ላይ ነበር።












