ቲክቶክ ከተጠቃሚዎች መረጃ ሰብስቧል በመባሉ ካሳ ለመክፈል ተስማማ

ቲክቶክ ሰው ሰራሽ ልህቀት [አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ] ተጠቅሞ ከተጠቃሚዎች መረጃ ሰብስቧል መባሉን ተከትሎ 92 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ለመክፈል ተስማማ።

አንድ ቡድን፤ ቲክቶክ ከተጠቃሚዎች መልክ ላይ ዕድሜ፣ ፆታና የዘር ሐረግ የሚለይ ቴክኖሎጂ በመጠቀሙ ሕግን ጥሷል ሲል ከሶ ነበር።

ቡድኑ እንደሚለው የተጠቃሚዎች መረጃ ወደ ቻይና ጭምር ተልኳል።

ቲክቶክ የቱንም ድርጊትን አላደረግኩም ሲል ቢያስተባብልም ካሳ የከፈለው ወደ ፍርድ ቤት ከመሄድ ብሎ እንደሆነ አሳውቋል።

ክሱን ያቀረበው ቡድን እንደሚለው 'ፌሺያል ሪኮግኒሽን' [የተጠቃሚዎች የፊት ገፅታ መለየት] የተባለውን ቴክኖሎጂ ቲክቶክ ተጠቅሞ መረጃ ሰብስቧል።

ይህ ያደረገበት አንደኛው ምክንያት ደግሞ የትኛውን ማስታወቂያ ለየትኞቹ ተጠቃሚዎች እንልቀቅ የሚለውን ለመለየት እንዲያመቸው ነው።

በዚህ ክስ ዙሪያ መግለጫ የሰጠው ቲክቶክ "የቀረቡብን ክሶች ብናስተባብልም ረዥም ወደሆነ የፍርድ ቤት ውሎ ከመሄድ ለቲክቶክ ማሕበረሰብ ደህንነቱ የተጠበቀና አስደሳች መድረክ መፍጠር ላይ ትኩረታችንን ማድረግ እንፈልጋለን" ብሏል።

ጉዳዩ አሜሪካ ውስጥ ባለ የፌዴራል ፍርድ ቤት ታይቶ ቢሆን ኖሮ ገንዘቡን አሜሪካዊያን የቲክቶክ ተጠቃሚዎች ይከፋፈሉት ነበር።

ቲክቶክ ላይ የቀረበው ክስ የተሰማው በአሜሪካዋ ኢሊኖይ ግዛት ነው። ግዛቲቱ ከበይነ መረብ የሚሰበሰብ መረጃን በተመለከተ ጥብቅ ሕግ አላት።

ቲክቶክ 'ፕራይቬሲ ፖሊሲው' [ከተጠቃሚዎች ጋር በሚገባ ስምምነት] ላይ የሰዎችን መረጃም ሆነ አድራሻ እንደሚሰበስብ አሊያም እንደማያሰበስብ፤ አልፎም መረጃ ከአሜሪካ ውጭ እንደሚያስቀምጥ አሊያም እንደማያስቀምጥ በግልፅ ለማስፈር ተስማምቷል።

ፕሮፕራይቬሲ የተሰኘው የግል ድርጅት ባለሙያ የሆኑት ሬይ ዋልሽ "ቲክቶክ ይህን ያክል ገንዘብ ለመክፈል የተስማማው ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ቢሄድ እንደማያሸንፍ ስለገባው ነው" ይላሉ።

"እርግጥ ነው ቲክቶክ ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ ለመፋለም የሚያስችል ገንዘብ አለው። ነገር ግን በጣም ብዙ በመክፈል ክሱን መሸፋፈን መርጧል። የኩባንያው ቻይናዊ ባለቤት ባይትዳንስ ገንዘብ ከስሮም ቢሆን ይህንን ጉዳይ ከመገናኛ ብዙሃን አፍ ማውጣትን የተሻለ አማራጭ አድርጎታል።"

ባይትዳንስ የተሰኘው የቲክቶክ እናት ኩባንያ መሰል ክስ ሲቀርብበት ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

በፈረንጆቹ 2019 ከታዳጊ ተጠቃሚዎች ላይ መረጃ ሰብስቧል የሚል ክስ ቀርቦበት ነበር።

ነገር ግን ኩባንያው ምንም ዓይነት መረጃ ከአሜሪካ ወደ ቻይና አላኩም ሲል በተደጋጋሚ ያስተባብላል።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ቲክቶክ መረጃ ወደ ውጭ ሃገር በመላክ የሃገራችንን ደህንነት አደጋ ላይ ጥሏል በሚል ነበር መተግበሪያውን [አፕሊኬሽን] ከማውረጃ ገፆች ያገዱት።