ሻሚማ ቤገም፡ አይኤስን የተቀላቀለችው ተማሪ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እንዳትመለስ ብይን ተሰጠ

የፎቶው ባለመብት, BBC News
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ፍርድ ቤት እስላማዊ ታጣቂ ቡድን [አይኤስ]ን የተቀላቀለችው ተማሪ ስለዜግነቷ ለመከራከር ወደ አገሪቷ መመለስ እንደማትችል ብይን ሰጠ።
ሻሚማ አይ ኤስን ለመቀላቀል ወደ ሶሪያ ያቀናቸው ታዳጊ ሳለች ነበር።
ፍርድ ቤቱ በአንድ ድምፅ ባሳለፈው ውሳኔ፤ ለመመለስ ፈቃድ ባለማግኘቷ መብቷ አልተጣሰም ብሏል።
የ21 ዓመቷ ሻሚማ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር የእንግሊዝ ዜግነቷ እንዲነሳ ያሳለፉትን ውሳኔ ለመከራከር ወደ ዩኬ መመለስ ትፈልጋለች።
ሻሚማ አሁን የምትገኘው በሰሜን ሶሪያ በታጣቂዎች በሚጠበቅ ካምፕ ውስጥ ነው።
ሻሚማ እርሷ እና ሁለት የኢስት ለንደን ተማሪዎች እአአ በ2015 እስላማዊ ታጣቂ ቡድኑን ለመቀላቀል ዩኬን ለቀው ወደ ሶሪያ ሲጓዙ የ15 ዓመት ታዳጊ ነበረች።
እአአ በ2019 የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሳጂድ ጃቪድ፤ የብሔራዊ ደህንነት ሕግን መሰረት በማድረግ የሻሚማን ዜግነት ሰርዘዋል።
ባለፈው ሐምሌ ወር የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ፍትሐዊ የሆነው ብቸኛው አማራጭ ሻሚማ ወደ ዩኬ እንድትገባ መፍቀድ እንደሆነ ውሳኔ አሳልፎ ነበር።
ፍርድ ቤቱ ለዚህ ያስቀመጠው ምክንያት ካለችበት በሰሜናዊ ሶሪያ ከሚገኝ ካምፕ ሆና በተላለፈባት ውሳኔ ላይ ይግባኝ ማለት አልቻለችም የሚል ነበር።
የአገር ውስጥ መስሪያ ቤቱ ግን እርሷን ወደ ዩኬ እንድትመለስ መፍቀድ በብሔራዊ ደህንነት ላይ አደጋ ሊኖረው ይችላል በሚል በተደጋጋሚ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፤ የይግባኝ ሰሚ ፍርድቤቱ ያሳለፈውን ብይን በድጋሜ እንዲመረምር ጠይቋል።
አርብ ዕለት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚደንት ሮበርት ጆን ሪድ፤ መንግሥት ሻሚማ ወደ ዩኬ እንዳትመለስ የማድረግ መብት አለው ብለዋል።
ፕሬዚደንቱ የፍርድ ቤቱን ውሳኔው ሲያሳውቁም "ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ያቀረቡትን ይግባኝ ተቀብሎ ፤ የሻሚማን አቤቱታ ውድቅ አድርጓል" ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ የአንድ ግለሰብ መብት በፍትሐዊ መልኩ እንዲሰማ ሲደረግ ከብሔራዊ ደህንነት መርሆች ጋር በሚጋጭበት ጊዜ፤ የመሰማት መብቷ የበላይ መሆን አለበት የሚል የተሳሳተ እምነት ነበረው ሲሉም ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ብይን ውድቅ አድርገዋል።
ፍትሐዊ የመሰማት መብት እንደ የሕዝብ ደህንነት ባሉ ጉዳዮች አልተደፈረም ሲሉም አክለዋል።
የሻሚማን ጉዳይ የሚከታተለው ሊበርቲ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን አሁን የተሰጠውን ፍርድ "እጅግ አደገኛ ምሳሌ " ብሎታል።
ሻሚማ ቤገም ማን ናት?
ሻሚማ ከባንግላዴሽ ቤተሰቦቿ የተወለደችው በዩናይትድ ኪንግደም ነው።
ከሁለት የትምህርት ቤት ጓደኞቿ ጋር በመሆን አይኤስን ለመቀላቀል ወደ ሶሪያ ያመራችው የ15 ዓመት ታዳጊ ሳለች ነበር።
ሻሚማ ራቃ ወደሚገኘው የአይ ኤስ ዋና መስሪያ ቤት ያቀናችው በቱርክ አድረጋ ነበር። እዚያም ሆላንዳዊ መልማይ አገባች።
በአይኤስ ቁጥጥር ሥርም ከሦስት ዓመታት በላይ ኖራለች።
ከዚያም እአአ በ2019 በሶሪያ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ የዘጠኝ ወር ነፍሰጡር ሆና ተገኝታለች።
ህጻኑ በኋላ ላይ በሳምባ ምች በሽታ ሕይወቱ አልፏል።
ሻሚማ እንደምትለው ከዚህ በፊት ሁለት ልጆቿን አጥታለች።















