የዓለማችን ሃብታሙ ድርጅት አፕል ባለፉት 6 ዓመታት 100 ኩባንያዎች ገዝቷል።

ቲም ኩክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቲም ኩክ

አፕል ባለፉት 6 ዓመታት ብቻ 100 ኩባንያዎች መግዛቱን ዋና ኃላፊው ቲም ኩክ አሳውቀዋል።

ይህ በሳምንትኛ ሲሰላ አፕል በሦስትና አራት ሳምንታት ውስጥ አንድ ኩባንያ ይገዛል ማለት ነው።

ቲም ኩክ ይህን ይፋ ያደረጉት በኩባንያው ዓመታዊ የአክሲዮን ባለድርሻዎች ስብሰባ ላይ ነው።

አፕል በቅርቡ ከተመሠረተ ጀምሮ ከፍተኛ የተባለውን የሩብ ዓመት ትርፍ አጋብሷል። ድርጅቱ ያተረፈው ገንዘብ 111 ቢሊዮን ዶላር ነው።

ይህ ከኢትዮጵያ የ2013 ዓመታዊ በጀት የላቀው ትርፍ የገባው በፈረንጆቹ 2021 የመጀሪያ ሩብ ዓመት ብቻ ነው።

ቲም ኩክ ለባለአክሲዮኖች እንደተናገሩት አብዛኛዎቹ ድርጅቱ የገዛቸው ኩባንያዎች ቴክኖሎጂ ነክና ፈጠራን የተላበሱ ናቸው።

አፕል ከገዛቸው ኩባንያዎች መካከል ትልቁ የሚባለው በራፐርና ሙዚቃ አቀናባሪ ዶክተር ድሬ የተሠራው ቢትስ ኤሌክትሮኒክስ ነው።

አፕል ይህን ምርት የገዛው በ3 ቢሊዮን ዶላር ነው።

ሌላኛው ደግሞ ሰዎች የጠፋባቸውን ሙዚቃ የሚያስታውሰው ሻዛም የተሰኘው ሶፍትዌር ነው።

አፕል ይህን ኩባንያ በ2018 የገዛው በ400 ሚሊዮን ዶላር ነው።

ሀብታሙ አፕል ብዙ ጊዜ አነስተኛ የቴክኖሎጂ ተቋማትን ገዝቶ ከራሱ ምርቶች ጋር ይደባልቃቸዋል።

ሹፌር አልባ ተሸከርካሪ፣ ፖድካስትና ሌሎች

አፕል ባለፉት ስድስት ዓመታት የገዛቸው ኩባንያዎች ስብጥር ዝርዝር ረዘም ያለ ነው።

ባለፈው ዓመት አፕል በርካታ የሰው ሰራሽ ልህቀት [አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ] ኩባንያዎችን ገዝቷል።

ቨርቱዋል ሪያሊቲ [እውነታን ዓይናችን ላይ በተተከለ መሣሪያ የሚከስት]፣ የበይነ መረብ ክፍያ መንገዶች እንዲሁም ፖድካስት [የበይነ መረብ ሬዲዮ ፕሮግራሞች] ድርጅቱ ከገዛቸው ኩባንያዎች መካከል ናቸው።

በ2019 አፕል አሽከርካሪ አልባ የታክሲ ተቋም መግዛቱ ይታወሳል። አፕል ይህን ድርጅት የገዛው ሹፌር አልባ የየብስና የአየር ተሽከርካሪዎች ለመሥራት የያዘውን ትልም ለማሳካት ነው።

ሀብቱ ሁለት ትሪሊየን ዶላር ገደማ የሚገመተው አፕል ኩባንያዎችን ገዝቶ የራሱ ለማድረግ የሚያግዘው ተቆጥሮ የማያልቅ ገንዘብ ያለው ድርጅት ነው።

አፕል ባለፉት ስድስት ዓመታት 100 ኩባንያዎችን የገዛው ገንዘብ ስላለው ብቻ ሳይሆን አዋጭነታቸውን አይቶ ነው ይላሉ የዘርፉ ሰዎች።

ከሌሎች ግዙፍ ድርጅቶች ጋር ሲነፃፀር አፕል ኩባንያዎችን ለመግዛት ያወጣው ወጪ ዝቅ ያለ ነው።

ለምሳሌ ማይክሮሶፍት ሊንክዲን የተሰኘው ኩባንያ የገዛው በ26 ቢሊየን ዶላር ነው። አማዞን ለሆል ፉድስ 13.7 ቢሊየን፤ ፌስቡክ ደግሞ ለዋትስአፕ 19 ቢሊየን ዶላሮች አውጥተዋል።

አፕል ከገዛቸው 100 ኩባንያዎች ቁንጮ የሚባሉት አስሩ እንኳ ቢደመሩ ወጪያቸው ከላይ ከተጠቀሱት ያነሰ ነው።