አማድ ዲያሎ - ቀጣዩ ሳሙኤል ኤቶ?

አይቮሪ ኮስታዊው አዲሱ የማንቸስተር ዩናይትድ አማድ ዲያሎ፣ ከኮከብ አፍሪካዊያን ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ሳሙኤል ኤቶን ይተካል እየተባለ እየተሞካሸ ነው።

ዲያሎ፤ ከጣልያኑ ክለብ አትላንታ ወደ እንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ኃያሉ ዩናይትድ በጥር ወር የዝውውር መስኮት ነው የመጣው።

ዲያሎ ከኤቶ አልፎ በጣሊያን ሴሪ-አ ለሮማ፣ ለፓርማ ከተጫወተው ሌላኛው አይቮሪ ኮስታዊ ዠርቪንሆ ጋር እየተነፃፀረ ነው።

ለዩዲኒዜና ቬሮና ለአስር ዓመታት ያክል የተጫወተው ኢማኑኤል ባዱ "ዲያሎ የአፍሪካ ከዋክብትን ብቃት አጣምሮ የያዘ ነው" ሲል ለቢቢሲ አፍሪካ ስፖርት ይናገራል።

"ኳስ ይዞ በመጫወት ረገድ የሳሙኤል ኤቶን ብቃት ይዟል። ኳስ መያዝ እንዴት እንዳለበት ያውቃል። ደግሞ ኳስ ሲያቀብል ድንቅ ነው። ወደ ፍጥነት ስንመጣ ደግሞ ልክ እንደ ዠርቪንሆ ነው።"

ሳሙኤል ኤቶ አራት ጊዜ የአውሮፓ ቻምፒዬንስ ሊግ ዋንጫ አንስቷል። ሶስት ጊዜ ደግሞ ከባርሴሎና ጋር የላሊ ጋ ክብር ማግኘት ችሏል። በአህጉር ደረጃ ደግሞ ሁለት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤት መሆን የቻለ ድንቅ ታሪክ ያለው ተጫዋች ነው፤ ኤቶ።

አራት ጊዜ የአፍሪካ ኮከብ ተብሎ የተመረጠው ኤቶ ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ሕይወቱን ሀ ብሎ የጀመረው በላሊ ጋ ነው። በወቅቱ 16 ዓመቱ ነበር። ዲያሎ ደግሞ በ17 ዓመቱ ነው በሴሪ አ መታየት የጀመረው።

"ገና 18 ዓመቱ ስለሆነ ጫና ልናሳድረበት አይገባም። ነገር ግን የሚፈልገውን ነገር እንዲያደርግ ሊፈቅደለት ይገባል" ይላል ባዱ።

ከጋና ብሔራዊ ቡድን በፈረንጆቹ 2009 ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫን ማንሳት የቻለው ባዱ "አንድ ሁለት ነገር እያሳዩ ልጁን እንዲያድግ ማድረግ ነው የሚያሻው። ይህ ከሆነ በሚቀጥሉት ዓመታት በአፍሪካ ከምናያቸው ድንቅ ተጫዋቾች መካከል መሆኑ አይቀርም" ይላል።

አማድ ዲያሎ ለዩናይትድ ከ23 ዓመት በታች ተሰልፎ በተጫወተበት ጨዋታ 2 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል። በጨዋታው የዩናይትድ ወጣቶች የሊቨርፑል አቻዎቻቸውን 6-3 ረምርመዋል።

ዲያሎ ከአትላንታ ጋር በነበረው ቆይታ ለዋናው ቡድን ሶስት ጊዜ ተሰልፎ ተጫውቷል። ከእነዚህ መካከል አንደኛው ባዱ ከወር በፊት የተሰናበተው ቡድን ሄላስ ቬሮና ጋር ያደረገው ግጥሚያ ነው።

የ30 ዓመቱ ባዱ፤ ዲያሎን ከክሪስቲያኖ ሮናልዶ ጋር ማነፃፀር ተገቢ ነው ብሎ አያስብም። ክሪስትያኖ ወደ ዩናይትድ በመጣበት ወቅት የክንፍ ተጫዋች እንደነበር የሚያስታውሰው ባዱ፤ ዲያሎም የክንፍ ተጫዋች መሆኑ ብቻ ከሮናልዶ ጋር ሊያነፃፅረው አይገባም ባይ ነው። ብዙዎች ዲያሎን ከሮናልዶ የሚያነፃፅሩት በ18 ዓመታቸው ዩናይትድን በመቀላቀላቸው ምክንያት ቢሆንም ባዱ ግን ይህ ፍትሃዊ አይደለም ይላል።

ባዱ፤ ዲያሎ ልክ እንደ ክርስቲያኖ ለፕሪሚዬር ሊጉ የሚመጥን አካላዊ ጥንካሬ ገና አላዳበረም ብሎ ያስባል።"ሮናልዶ ስፖርቲንግ ሊዝበን ሳለ 25 የሊግ ጨዋታዎች አድርጓል። ዲያሎ ግን ለአትላንታ ዋናው ቡድን ብዙ ጨዋታዎች አላደረገም" ሲል ያብራራል። "ነገር ግን የሚያመሳስላቸው ነገር ብዙ ነው። ለምሳሌ ዕድሜያቸውና የመጡበት ዋጋ ተመሳሳይ ነው። ቢሆንም ሁለቱን ለማነፃፀር ጊዜው ገና ነው ብዬ ነው የማምነው።"

አማድ ትራኦሬ በተሰኘ ስሙ ይታወቅ የነበረው ዲያሎ ለአትላንታ ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ሁለት ጎሎች ማስቆጠሩ ይታወሳል። ከዩናይትድ ዋናው ቡድን ጋር ልምምድ ማድረግ የጀመረው ዲያሎ ከአሠልጣኝ ኦሌ ጉናር ስልሻዬር አድናቆት ማግኘት ችሏል። "ረጋ ብሎ ብቃቱን ማንፀባረቅ እንዲችል ጊዜ እንሰጠዋለን" ሲል ሶልሻዬር ለወጣቱ ያለውን ሕልም ተናግሯል።

ዲያሎ፤ በ18 ዓመቱ ለዩናይትድ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ማርከስ ራሽፈርድ ይለብስ የነበረው 19 ቁጥር ማሊያ ተሰጥቶታል።