ትግራይ፡ በማይካድራ ግድያ ከተጠረጠሩት መካከል 36ቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ

ጥቃቱ ተፈጸመ የተባለበት ማይካድራ ከሁመራ ከተማ በቅርብ እርቀት ላይ ትገኛለች

ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በማካይድራ የሰዎች ግድያ ላይ የተሳተፉ 279 ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን ከተሰበሰቡ መረጃዎች መረዳት እንደቻለ ገለፀ።

አቃቤ ሕግ በትናንትናው ዕለት ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመሆን መግለጫ የሰጠ ሲሆን ከተጠርጣሪዎች መካከልም 36ቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል።

በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሙስና እና የተደራጁ ወንጀል ጉዳዮች ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ፍቃዱ ጸጋ እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል እና የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ዘላለም መንግስቴ በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ አብዛኞቹ ተጠርጣሪዎች ወደ ሱዳን ማምለጣቸውን ተናግረዋል።

በማይካድራ ጥቃት የተፈፀመው በፌደራል መንግሥትና በሕወሓት ኃይሎች መካከል ጥቅምት 24፣ 2013 ዓ.ም ግጭት ከተቀሰቀሰ ጥቂት ቀናት በኋላ፤ ጥቅምት 30፣ 2013 ዓ.ም ሰኞ ዕለት ሲሆን የሰብአዊ መብት ቡድኖች በጥቃቱ ከ600 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ጥቃቱ የተፈፀመው ጥቅምት 30፣ 2013 ዓ. ም ከሰዓት በኋላ 9፡ 00 ሰዓት ላይ የነበረ ሲሆን አስከሚቀጥለው ቀን ጠዋት ድረስ መቀጠሉን ነዋሪዎቹ በወቅቱ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ከዚህ ጥቃት ጋር በተያያዘ የሟቾችን ቁጥር ለማወቅ ከጤና ሚኒስቴር የሀኪሞች ቡድን ተልኮ፤ 117 ጉድጓዶች የተገኙ ሲሆን አስክሬኖችን መርምሮ የሟቾቹን ብዛት እና የሞት ምክንያት ለማወቅ እየተሰራ መሆኑን አቶ ፍቃዱ ገልፀዋል።

አቶ ፍቃዱ አክለውም፤ ይህ የሕክምና ባለሙያዎች ቡድን ሪፖርት እስኪደርስ ድረስ ትክክለኛው በጥቃቱ የሞቱ ሰዎችን ብዛት መግለጽ እንደማይቻል አስታውቀው "መሬት ባለው እውነት እና በየሚዲያው የተገለጸው" መካከል ልዩነት መኖሩን በማብራሪያቸው አስረድተዋል፡፡

የማይካድራ ከተማ በትግራይ ክልል ደቡብ ምዕራብ ዞን የምትገኝ ስትሆን ጥቅምት 24፣ 2013 ዓ. ም ሕወሓት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ግጭት ውስጥ ከገባ በኋላ በርካታ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው ይፋ ተደርጎ ነበር።

በወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኃላፊ ሚሼል ባችሌት በማይካድራ ከተማ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት ተገድለዋል የሚለው ሪፖርት እንዲጣራ ጠይቀው ነበር።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በወቅቱ ባወጣው ሪፖርት ጥቃቱን ማን እንደፈጸመው ለማረጋገጥ አለመቻሉን አመልክቷል። ነገር ግን ያነጋገራቸው የአይን እማኞች ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ጋር የሚዋጉትን የህወሓት ታማኝ ኃይሎች ይከስሳሉ።

አምነስቲ ኢንትርናሽናል በማይካድራ ስለተፈጸመው ነገር ለማረጋገጥ ከጥቃቱ በኋላ ወደ ስፍራው የሄዱ እማኞችን ያነጋገረ ሲሆን፤ በከተማዋ ውስጥ በየቦታው የወደቁ አስከሬኖችንና ከጥቃቱ ቆስለው የተረፉ ሰዎችን እንደተመለከቱ ተናግረው ነበር።

አብዛኞቹ አስከሬኖች የተገኙት በከተማዋ ማዕከላዊ ክፍል ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሚገኝበት አካባቢና በአቅራቢያው ወደምትገኝ የሁመራ ከተማ የሚያመራውን መንገድ ተከትሎ መሆኑን የአይን እማኞችና የተገኙት ምስሎች ጠቁመዋል።

ሪፖርቱ በወጣበት ወቅት የትግራይን ክልል እያስተዳደሩ የነበሩት ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ውንጀላዎቹን "መሰረት የሌላቸው ናቸው" ማለታቸውን አጃንሰ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቦ ነበር።

የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪው ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንዳለው በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በምትገኘው ማይካድራ ከተማ ውስጥ በተፈጸመው በዚህ ጥቃት ቁጥራቸው በመቶዎች ሊቆጠሩ የሚችሉ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት ተገድለዋል።

ድርጅቱ ከማይካድራ ከተማ የወጡና በየቦታው ወድቀው የሚታዩ አስከሬኖችን የሚያሳዩ አሰቃቂ ፎቶግራፎችንና ቪዲዮዎችን በመመርመር ምስሎቹ የቅርብ ጊዜና ስፍራውም ማይካድራ መሆኑን ለማረጋገጥ መቻሉን ገልጾ ነበር።

በአገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ተፈጸመ የተባለውን ጥቃት ተከትሎ ለወራት በውዝግብ ውስጥ ቆይተው የነበሩት የፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ክልል አስተዳደር ጥቅምት 24፣ 2013 ዓ. ም ወደ ግልጽ ጦርነት መግባታቸው ይታወሳል።

የፌደራል መንግሥቱ መቀሌን ከተቆጣጠረ በኋላ ጦርነቱ መጠናቀቁን የገለፀ ቢሆንም አሁንም ግን በተለያዩ አካባቢዎች ውጊያ እንደሚካሄድ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድርጅቶች በሪፖርታቸው እየገለፁ ነው።

ከዚህ ግጭት ጋር በተያያዘ 60 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ወደ ሱዳን ሲሸሹ በሚሊዮኖች ሚቆጠሩ ደግሞ በአገር ውስጥ ተፈናቅለው የሰብዓዊ እርዳታ እየጠበቁ ይገኛሉ።

በትግራይ አሁንም የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ያልተመለሰ ሲሆን የሰብዓዊ ርዳታ ድርጅቶችም እርዳታ ለሚፈልጉ ለማድረስ እንደልብ መንቀሳቀስ አለመቻላቸውን በመግለጽ ተደጋጋሚ መግለጫ አውጥተዋል።