ጭንቅላቱን ከአዞ አፍ ፈልቅቆ በማውጣት ራሱን ያተረፈው አውስትራሊያዊ

ግለሰበዑ ጥቃት የደረሰበት በሳልት ወተር አዞ መሆኑን ተናግሯል

አውስትራሊያ ውስጥ በአዞ የተነከሰው ግለሰብ ጭንቅላቱን ከአዞው አፍ ውስጥ ፈልቅቆ በማውጣት ሕይወቱን ማትረፉን የጤና ባለሙያዎች ተናገሩ።

ግለሰቡ 44 ዓመቱ ነው የተባለ ሲሆን በክዊንስላንድ ፕላሲድ ሀይቅ ውስጥ እየዋኘ እንደነበር የሕክምና ባለሙያዎቹ አክለው ተናግረዋል።

ግለሰቡ ላይ ጥቃት ያደረሰው አዞ ከ1.5 ሜትር እስከ 2 ሜትር ድርስ ርዝማኔ እንዳለው ተገልጿል።

ወደ ሆስፒታል በተወሰደበት ወቅት ቀለል ያሉ ጉዳቶች እንደነበሩበት ሀኪሞቹ ተናግረዋል።

የአካባቢው ባለሥልጣናት ግለሰቡ ተጨማሪ ጉዳት ሳያጋጥመው ህይወቱ በመትረፉ እድለኛ ነው ብለዋል።

የድንገተኛ ጊዜ የሕክምና ባለሙያዎች ጉዳቱ በደረሰበት ዕለት ሐሙስ፣ እነርሱ በስፍራው ሲደርሱ "እጅጉን ተረጋግቶ" እንደነበር መስክረዋል።

"እርሱ እንደ ነገረን ከሆነ አዞው ጭንቅላቱን ነከሰው። እናም ጭንቅላቱን ለማስለቀቅ በሚያደርገው ጥረት እጁን ወደ አዞው አፍ ያስገባ እና የፈለቀቀው ሲሆን በዚህም የአመልካች ጣቱን አጥቷል" ሲሉ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።

ግለሰቡ ጥቃት ከደረሰበት በኋላም ወደ ሐይቁ ዳርቻ ለመምጣት ረዥም ርቀት ዋኝቶ፣ ራሱን ወደ ዳርቻው በማውጣት የአስቸኳይ ጊዜ ሰራተኞች እስኪደርሱለት ድረስ ጠብቋል።

ሐኪሙ አክለውም "በኛ ምርመራ መሰረት ጭንቅላቱ ላይ ጉዳት የደረሰበት ምልክት ይታያል" ብለዋል።

ግለሰቡ የተወሰደው ወደ ካሪንስ ሆስፒታል ሲሆን ቢቢሲ ከሆስፒታሉ ኃላፊዎች ማረጋገጥ እንደቻለው በተረጋጋ ሁኔታ እና በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛል።

ግለሰቡ ማንነቱ እንዳይገለፅ የተጠየቀ ሲሆን በሀይቁ ላይ ከዚህ በፊት ላለፉት ስምነት ዓመታት በሳምንት ሶስት ጊዜ ይዋኝ ነበር ተብሏል።

ሀኪሙም "ወደ ሀይቁ በሌላ ጊዜ በመሄድ ዳግም ቢዋኝ የሚገርም አይሆንም " በማለትም ያለውን ልምድ አስረድተዋል።

የክዊንስላንድ አካባቢ ጥበቃ ወደ ስፍራው ባለሙያዎችን የላከ ሲሆን "የደረሰው አደጋ ምን መልክ እንዳለው ለማጥናት እንዲሁም ተጨማሪ እርምጃዎች መውሰድ ያስፈልግ እነደሆን ለመለየት" እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

በሰሜናዊ ክዊንስላንድ ውሃማ አካባቢዎች አዞዎች በብዛት ይገኛሉ።