89 ቱሪስቶች በታይላንድ በቁጥጥር ስር ዋሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የታይላንድ ፖሊስ የኮሮናቫይረስ ገደቦችን ጥሰው በኮህ ፋንጋን ደሴት መጠጥ ቤት ውስጥ ሲዝናኑ የነበሩ 89 የውጪ ዜጎችን በቁጥጥር ሥር አዋለ።
በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች ዩኬን እና አሜሪካን ጨምሮ የአስር አገራት ዜጎች ናቸው ተብሏል።
ታይላንድ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በሚል የእንቅስቃሴ ገደብ ጥላለች።
በአገሪቱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እየጨመረ ሲሆን እስካሁን ድረስ 15 ሺህ 465 ሰዎች መያዛቸው በምርመራ ሲረጋገጥ ከእነዚህም መካከል 76 ያህሉ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
የእንቅስቃሴ ገደቡ ከተጣለ ወዲህ ኮህ ፋንጋን ደሴት በሚገኝበት ሱራት ታኒ ግዛት 29 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መኖራቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ማክሰኞ ዕለት ፖሊስ ስሪ ስክስቲ ባር የተሰኘውን የመዝናኛ ስፍራ በድንገት ከከበበ በኋላ ባካሄደው አፈሳ የውጪ ዜጎቹ መያዛቸው ታውቋል።
ለፖሊስ ፍንጭ የሰጠው በኦንላየን (በበይነ መረብ) የተሸጠ የመግቢያ ትኬት መኖሩን መታወቁ ነው።
በኋላ ላይ የተለቀቁ ምስሎች እንደሚያሳዩት በመዝናኛ ስፍራው በርካታ ሰዎች የነበሩ ሲሆን አብዛኞቹ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አድርገው ነበር።
ፖሊስ እንዳለው የመዝናኛ ሥፍራውን ባለቤት እንዲሁም ዝግጅቱን ያሰናዳውን ግለሰብ ጨምሮ 22 የታይላንድ ዜግነት ያላቸው ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ፖሊስ የዝግጅቱ አዘጋጅ እና የመዝናኛው ባለቤት ያለፈቃድ በመስራት፣ ተዝናኞቹ ደግሞ የተቀመጠውን የእንቅስቃሴ ገደብ በመጣስ ይጠየቃሉ ብሏል።
የእንቅስቃሴ ገደቡን የጣሱ ግለሰቦች በሁለት ዓመት እስር አልያም 976 ዶላር ቅጣት ይጣልባቸዋል።
ኮህ ፋንጋን በባህር ዳርቻዎች አካባቢ ለሊቱን ሙሉ በሚካሄዱ የሙዚቃ ዝግጅቶች የምትታወቅ ሲሆን በአዲስ ዓመት ወቅት ከ30 ሺህ በላይ ቱሪስቶች ይጎርፉባታል።
ከባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ጀምሮ ቱሪስቶች ወደ ታይላንድ እንዳይገቡ ታግደዋል።
የውጪ አገራት ዜጎችን የእንቅስቃሴ ገደብ በመጣሳቸው ምክንያት ስትቀጣ ታይላንድ ብቸኛዋ አገር አይደለችም።
በኢንዶኔዢያ ባሊ ቱሪስቶች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ባለማድረጋቸው ፑሻ አፕ እንዲሰሩ ተደርገው በተንቀሳቃሽ ምስል ተቀርጾ ታይቷል።
የአገሪቱ ፖሊሶች ቱሪስቶቹ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ባለማድረጋቸው ብቻ 100 ሺህ ሩፒ እንዲከፍሉ ጠይቀው ባለመቻላቸው 50 ፑሽአፕ እንዲሰሩ አድርገዋቸዋል።
የፊት መሸፈኛ ጭምብል አድርገው ነገር ግን በተገቢው ሁኔታ ባለመሆኑ ደግሞ 15 ፑሻፕ የተቀጡ አሉ።












