የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካመላ ሐሪስ ማን ናቸው? የትስ ነው የሚኖሩት?

ካመላ ዛሬ አዲስ ታሪክ ጽፋለች፡፡ የመጀመርያዋ የአሜሪካ ሴት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆናለች፡፡

ለመሆኑ ማን ናት? ከየት መጣች? የት ነበረች? ምን ትወዳለች? ስለሷ ልናውቃቸው የሚገቡ ቁልፍ ጉዳዮች ከዚህ እንደሚከተለው ተከትበዋል፡፡

በዕድሜ 55 ብትደፍንም ለጊዜው አንቱታውን ትተን እንቀጥል፡፡

ካመላ ሐሪስ የተወለደችው በካሊፎርኒያ ግዛት ኦክላንድ ከተማ ነው፡፡

እናቷ ሻየመላ ጎፓላን ሕንዳዊት ናት፡፡ አባቷ ዶናልድ ሐሪስ ደግሞ ጃማይካዊ ነበሩ፡፡ አባትና እናቷ ሁለቱም በስደት ነው ወደ አሜሪካ የመጡት፡፡

ሁለቱም እንግሊዝ በቅኝ ከገዛቻቸው አገራት ነው የመጡት፡፡ ሁለቱም እንግሊዝ ሄደው እንዲማሩ ተጠይቀው አሜሪካንን የመረጡ ናቸው፡፡

በዩኒቨርስቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ በርክሌይ ካምፓስ ውስጥ ተማሪ ሆኑ፡፡

እሱ ኢኮኖሚክስ እሷ ሆም ሳይንስ ተማሪዎች ነበሩ፡፡

የጥናት ቡድን ውስጥ ተያዩ፡፡ ያኔ አባቷ በካሊፎርኒያ በርክሌይ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ ነበር፡፡ በ1960ዎቹ መጀመርያ መሆኑ ነው፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን ብሪቲሾች እንዴት አገሩ ጃማይካ ገብተው በቅኝ ግዛት ሕዝቡን እንዳሰቃዩ ንግግር ያደርግ ነበር አባቷ፡፡ ተማሪ እያለ ነው ይሄ ታሪክ፡፡

ንግግሩን ሲጨርስ አንዲት በጣም ደቃቃ ቀጭን ሴት፣ ነጠላ ጫማ የተጫማች፣ የሕንዶችን ነጠላ ከደረቷ ያጣፋች፣ ሄዳ ተዋወቀችው፡፡

ከሕንድ አገር እንደመጣችና እዚያም እንግሊዞች አገሬውን ፍዳውን ያበሉት እንደነበር ነገረችው፡፡ ተቀራረቡ፣ ተዋደዱ፣ ተጋቡ፡፡

መጀመርያ ካመላን ከዚያም ማያን ወለዱ፡፡

ካመላ ማያ የምትባል ታናሽ እህት አለቻት፡፡

አባቷ ዶናልድ ሐሪስ ከእናቷ ሻይመላ ጋር በኋላ ላይ በ1970ዎቹ መጀመርያ ተለያይተዋል፡፡ ያን ጊዜ ካመላ ገና የ7 ዓመት ሕጻን ነበረች፡፡

ካመላና ማያን በማሳደጉ ረገድ የእናቷ ሚና ትልቅ ነበር፡፡ ሆኖም አባቷ ከፍቺ በኋላ ለቤተሰቡ ቅርብ ሆኖ ነበር የቆየው፡፡

እናቷ በኋላ ላይ እንደ አባቷ 3ኛ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል፡፡ የሞቱት በ2009 ዓ.ም ሲሆን ለሞታቸው ምክንያት የደንዳኔ ካንሰር ነበር፡፡

አባቷ ዶናልድ አሁን የ82 ዓመት ዕውቅ የምጣኔ ሀብት "ኢምሬትስ ፕሮፌሰር" ሲሆኑ ከስታንፈርድ ዩኒቨርስቲ ጡረታ ወጥተው በራሳቸው የማማከር ሥራ ይሠራሉ፡፡

አባቷ በጃማይካ ቀልድ አያውቁም፡፡ ልጆቻቸው አገራቸውን እንዲወዱ፣ እንዳይረሱ ይፈልጋሉ፡፡

ሐሪስ በቅርቡ ጃማይካን ከእጸ ፋሪስ ጋር አገናኝታ በመቀለዷ ሽማግሌው አባቷ ቱግ ብለው ነበር፡፡

ካመላ ሐሪስ ባለትዳር ናት?

የካመላ ሐሪስ ባል ዳግ ይባላል፡፡ ሁለት ለቁም ነገር የበቁ ወንድና ሴት ልጆች አሉት፡፡ ኮል እና ኢላ ይባላሉ፡፡

ከቀድሞ ባለቤቱ ከክሪስቲን ማኪን ነው የወለዳቸው፡፡ አሁን 26 እና 21 ዓመት ሆኗቸዋል፡፡

የአባታቸውን ሚስት ‹እንጀራ እናት› ብለው መጥራት አልፈለጉም፡፡ ካመላን ቅጽል ስም አወጡላት፡፡ ‹ሞማላ› እያሉ ነው የሚያቆላምጧት፡፡ እንደ እናትም ናት ለማለትም ጭምር ነው፡፡

ካመላ ሐሪስ ከእንጀራ ልጆቿ ኮል እና ኢላ ጋር በጣም ቅርብ ናት፡፡

ባሏ ዳግ በአሜሪካ ታሪክ ሁለተኛው "ካልአዊ አባወራ" (ሰከንድ ጀንትለማን) ይሆናል ማለት ነው፡፡

ካመላ ጥቁር ኢሲያዊት አሜሪካዊት ናት፡፡ የብዙ ደም ቅልቅል መሆኗ እንደማይረብሻት፣ ራሷንም አንዲት ጠንካራ ሴት አሜሪካዊት አድርጋ እንደምትቆጥር ተናግራለች፡፡

ዳግና ሐሪስ የተጋቡት በ2014 ሳንታ ባርባራ ካሊፎርኒያ ውስጥ ነበር።

ካመላ ኮሌጅ የተማረችው የብዙ ጥቁሮች ትምህርት ቤት በሆነው ሐዋርድ ዩኒቨርስቲ ነው፡፡

ሐሪስ ለዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የዲሞክራቶች እጩ ለመሆን ሩጫ ጀምራ ኋላ ላይ በበቃኝ የወጣች ሴት ናት።

በውድድሩ ወቅት አሁን የምርጫ ሸሪክ ካደረጓት ጆ ባይደን ጋር በተደጋጋሚ ተጋጭተዋል፣ ተከራክረዋል፣ አንድ ሁለት ተባብለዋል። በቀጥታ የክርክር ሥርጭት ወቅት ባይደንን አፋጣቸዋለች፡፡

የላይኛው ምክር ቤት አባል ሆና ካሊፎርኒያን ስትወክል በስብሰባዎች ላይ ትንፋሽ የሚያሳጥሩ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ትታወቃለች፤ ሐሪስ፡፡

በካሊፎርኒያ ግዛት ዐቃቤ ሕግ ሆና ስትሰራ ስኬታማ አዳዲስ አሰራሮችን ዘርግታለች ተብላ ትሞካሻለች።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጆ ባይደን ሐሪስን የምርጫ ሸሪክ አድርገው ስለመምረጣቸው አስተያየት እንዲሰጡ በተጠየቁ ጊዜ፣ እንደመጣላቸው ስለሚናገሩ ይመስላል፣ "ባይደን አስቀያሚ ሴት ነው የመረጠው፤ ምን ነካው ባይደን? በምርጫው ተደንቂያለሁ" ብለው ነበር።

ዛሬ ባይደንና ሐሪስ ትራምፕና ፔንስን አባረው ሥልጣኑን በይፋ ይረከባሉ፡፡

ሐሪስ በፊት የካሊፎርኒያ አቃቤ ሕግ ነበረች። በአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ካሊፎርኒያን በመወከል የተሳተፈችበት ዘመን ስኬታማ ነበር፤ ጠንካራ ሴት መሆኗን ያስመሰከረችበት ነበር፡፡ አሁን ያን ምክር ቤት በሊቀመንበርነት ትዘውረዋለች።

ሐሪስ በፊት በሳንፍራንሲስኮም የአንድ ቀጠና አቃቢ ሕግ ሆና ሠርታለች።

ሃሪስ ለባይደን በምርጫ ውስቀሳ ወቅት 2 ሚሊዮን ዶላር በበይነ መረብ ገንዘብ ማሰባሰብ ችላ ነበር፤ በግዛቷ ካሊፎርኒያ።

ከጆርጅ ፍሎይድ የግፍ ግድያ ጋር በተያያዘ ደግሞ ሐሪስ በትላልቅ ሰልፎች የሕዝብ ትኩረት ያገኙ ንግግሮችን አድርጋ ነበር።

የቀድሞዋ የካሊፎርኒያ ዐቃቤ ሕግ ሐሪስ በፀረ ዘረኝነት እንቅስቃሴ ውስጥ ድምጽ ስታሰማ ነው የኖረችው።

ገና የ7 ዓመት ሕጻን ሳለች እናትና አባቷ የጸረ ዘረኝነት ሰልፎች ላይ ይዘዋት እየሄዱ መፈክር እንድታሰማ ያደርጓት ነበር፡፡

ያ አድጎ ዛሬ ለጥቁሮች አለኝታ ሆናለች፡፡

በተለይም ሐሪስ በአሜሪካ ውስጥ የፖሊስ ክንድ በጥቁሮች ላይ መበርታቱን በመቃወም የፖሊስ ማሻሻያ እንዲደረግ ስትቀሰቅስ ትታወቃለች።

ካመላ ሐሪስ ዛሬ ታሪክ የምትጽፈው አንድ ብቻ አይደለም፡፡ የመጀመርያዋ ሴት፣ የመጀመርያዋ ጥቁር ሴት፣ የመጀመርያዋ ጥቁር እና ሴት እና ደቡብ ኢሲያዊት-አሜሪካዊት ሴት እያለ ይቀጥላል ዝርዝሩ፡፡

ምክትል ፕሬዝዳንት ሥራው ምንድነው?

በታሪክ እንደታየው የምክትል ፕሬዝዳንቱ ሥራና ኃላፊነት ብዙ የሚባል አይደለም፡፡

ባርባራ ፔሪ የፕሬዝዳንታዊ ጥናት ተመራማሪ ናቸው፡፡ በቨርጂኒያ ዩኒቨርስቲ ውስጥ፡፡ በአሜሪካ የምክትል ፕሬዝዳንቱ ሥራ ምንድነው ሲባሉ በአጭሩ እንዲህ መልሰው ነበር፡-

‹‹የምክትል ፕሬዝዳንቱ ሥራና ኃላፊነት የፕሬዝዳንቱን የልብ ትርታ ደረቱ ላይ ተለጥፎ እያዳመጡ መኖር ነው››

ባርባራ ማለት የፈለጉት ምንድነው?

የምክትል ፕሬዝዳንቱ ሚናና ጉልበት የሚገለጸው የፕሬዝዳንቱ ጤና ሲታወክ ወይም ደግሞ ሲሞት ብቻ ነው ማለታቸው ነው፡፡

በአሜሪካ ታሪክ ከ45 ፕሬዝዳንቶች ውስጥ ዘጠኙ የሥራ ዘመናቸውን ሳይጨርሱ ነጩን ቤተ መንግሥት ለቅቀዋል፡፡ ይህም ማለት ምክትሎቻቸው ትልቁን ሥልጣን ለመያዝና ለመሾፈር ዕድል አግኝተዋል ማለት ነው፡፡

ከዘጠኙ ታዲያ ስምንቱ በሞት ነው ከዋይት ሐውስ የወጡት፡፡

ባይደን 78 ዓመታቸው ነው፡፡ ሐሪስ በተጠንቀቅ መሆን አለባት ማለት ነው፡፡ አይበለውና አይቀሬው ሞት ቢመጣ የዓለም ትልቁ ሥልጣን ካመላ ሐሪስ እጅ ላይ ይወድቃል፡፡

የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ምክትላቸው እንዲሆኑ የሚመርጧቸው ሰዎች እነሱ የሌላቸውን የሚያሟሉ እንዲሆኑ ይሻሉ፡፡

ይሄን ነገር ጂሚ ካርተር ናቸው በ1970ዎቹ የጀመሩት ይባላል፡፡

ጂሚ የጆርጂያ ገዥ ነበሩ፡፡ ፖለቲካውን ብዙም አያውቁትም ነበር፡፡ ዋሺንግተን ዲሲ ትርቃቸው ነበር፤ ለዓይንም ለልብም፡፡

ሲያሸንፉ ጊዜ ታዲያ ዎልተር ሞንዳሌ የሚባሉ ሴናተርን ምክትላቸው አደረጉ፡፡ ዋልተር የዲሲን ፖለቲካ ቀረጣጥፈው የበሉ ሰው ነበሩ፡፡

ምን ለማለት ነው፤ ፕሬዝዳንቶችና ምክትሎቻቸው በብዙ ነገር መለያየት የርዕዮተ ዓለምና አካባቢያዊ ሚዛንን ለማስጠበቅ ይረዳል፡፡

ለምሳሌ ኦባማ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ብዙም የካፒቶል ሒልን ፖለቲካ አያውቁም ነበር፡፡ ጆ ባይደን የ35 ዓመት የፖለቲካ ልምድ የነበራቸው ሴናተር ነበሩ፡፡ ምክትላቸው አደረጓቸው፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎቻቸውን ይበልጥ ለመሳብ ኢቫንጀሊካል አጥባቂ ክርስቲያን ተከታይ የሆኑትን ማይክ ፔንስን አመጡ፡፡

ጆ ባይደን ደግሞ ጥቁሮችንና ሴቶችን ወደፊት ማምጣት ነበረባቸው፡፡

ደጋፊዎቻቸው ይህን እንዲያደርጉ ይጠብቁባቸዋል፡፡ በዚያ ላይ ከዕድሜያቸው ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ቅሬታ በወጣቷ ካመላ ሐሪስ ለማካካስ ሞክረዋል፡፡

ስለዚህ ሐሪስ ለጆ ባይደን የጾታ፣ የቀለምና የዕድሜ ሚዛን አስጠባቂ ናት ማለት እንችላለን፡፡

ሌላው ሐሪስን ከምክትል ፕሬዝዳንቶች ፍዝ ሚና የተለየ ሚና እንዲኖራቸው የሚያደርጋት በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ያለው የቁጥር መመጣጠን ነው፡፡

ምክትል ፕሬዝዳንቶች 100 አባላት ባሉት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ውስጥ ሊቀመንበር ሆነው ስብሰባ ይመራሉ፡፡

ዘንድሮ ይህ ሚና መዶሻ መያዝ ብቻ አይሆንም፡፡

ወሳኙ ድምጽ የሚመጣው ከካመላ ሐሪስ ነው፡፡ ምክንያቱም በቁጥር ዲሞክራቶች 50፣ ሪፐብሊካኖችም 50 በመሆናቸው ነው፡፡ የመለያ የፍጹም ቅጣት ምቱን የሚመቱት ካሜላ ሐሪስ ናቸው፡፡

ካመላ ሐሪስ የት ነው የሚኖሩት?

ጆ ባይደን ነጩ ቤተ መንግሥት ቢሮም መኝታም ይሆናቸዋል፡፡ ለመሆኑ ምክትላቸው ካመላ ሐሪስ የት ነው የሚኖሩት?

ሐሪስና ባለቤታቸው ደግ ሌላ ቦታ ነው የሚኖሩት፡፡

በ19ኛው ክፍለ ዘመን በተሰራ እጅግ ግዙፍና ውብ ቤት ውስጥ ነው መኖርያቸው የሚሆነው፡፡

ቤቱ የሚገኘው በሰሜን ምዕራብ ዋሺንግተን ሲሆን የአሜሪካ የናቫል አብዘርቫቶሪ ግቢ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡

ይሄ ግቢ ከዋይት ሐውስ ብዙም አይርቅም፡፡

የሐሪስ ቢሮ ደግሞ ዋይት ሐውስ ውስጥ ነው፡፡

ባለቤታቸው ሚስተር ዳግ የሚያስተምሩት በጆርጅታውን ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ጠበቃም ናቸው፡፡

ስለዚህ ለባልና ሚስቱ አዲሱ መኖርያ ቤታቸው ለሥራም ቅርብ ሆነ ማለት አይደል?

ባልና ሚስቱ ልጆቻቸውን ይዘው ወዲያ ወዲህ ማለት ሲፈልጉ ኤይርፎርስ-2 እና ቦይንግ 757 በተጠንቀቅ ሁልጊዜም ይጠብቃቸዋል፡፡

24 ሰዓት ሐሪስንና ባለቤታቸውን የሚጠብቅ ደኅንነት ለሰከንድ ዐይኑን አይጨፍንም፡፡

ሐሪስ እንደ ትራምፕ ጎልፍ የሚወዱ አይደሉም፡፡ ምግብ ማብሰል ግን ነፍሳቸው ነው፡፡ ምናልባት የጥቁር ነገር ሆኖ ሊሆን ይችላል ነገር ቀለል ማድረግ ይወዳሉ ይባላል፡፡

ጂንስና ኮንቨርስ ሸራ ጫማን ከታኮ ጫማ በበለጠ ታዘወትራለች ሐሪስ፡፡ እስከዛሬ ሦስት መጽሐፎችን ለኅመት ያበቃች ሲሆን አንዱ የልጆች መጽሐፍ ነው፡፡

‹እናቴ በዚያ ዘመን ስትወልደኝ እዚህ ትደርሳለች ብላ አስባ የምታውቅ አይመስለኝም› የምትለው ካመላ ሐሪስ ምናልባት የመጀመርያዋ የአሜሪካ ሴት ፕሬዝዳንት ሆና ሌላ ታሪክ ትጽፍ ይሆን?

ይህ እንዲሆን ደግሞ 4 ወይም 8 ዓመት መጠበቅ ላይኖርባት ይችላል፡፡ አይበለውና!