ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሜክሲኮው ፕሬዚዳንት አሜሪካ የስደተኞች ፖሊሲዋን እንድታሻሽል ጠየቁ
በሺዎች የሚቆጠሩ የመካከለኛው አሜሪካ ስደተኞች ቡድን በጓቲማላ ፖሊስ እንዳይወጡ በታገዱበት በአሁኑ ወቅት የሜክሲኮው ፕሬዚዳንት አንድሬ ማኑኤል ሎፔዝ ኦብራዶር አሜሪካ የስደተኛ ፖሊሲዋ ላይ መሰረታዊ ለውጥ እንድታደርግ ጠይቀዋል።
ፕሬዚዳንት አንድሬ በነገው ዕለት፣ ጥር 12/2013 ዓ.ም ስልጣን የሚረከቡት ተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በሰደተኞች ጉዳይ ላይ ከሜክሲኮም ሆነ ከሌሎች አገራት ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ ያላቸውን ተስፋ አስቀምጠዋል።
በአሁኑ ወቅት ወደ አሜሪካ የሚጓዙ በአብዛኛው መነሻቸውን ሆንዱራስ ያደረጉ 7 ሺህ የሚሆኑ የመካከለኛው አሜሪካ ስደተኞች ቡድን ወደ ጓቲማላ ገብተዋል።
በመቀጠልም ሜክሲኮን በመሻገር ወደ አሜሪካም ለመግባት ሰንቀዋል።
በየአመቱም ከመካከለኛው አሜሪካ የሚነሱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ካራቫን ተብሎ በሚታወቀው የጅምላ ቡድን የሚጓዙ ስደተኞች አብዛኛው በእግራቸው ወደ አሜሪካ በአንድ ላይ ይገባሉ።
ስደተኞቹ በአገራቸው ግጭት፣ ፖለቲካዊ መሳደድ፣ ጭቆናንና ድህነትን ሸሽተው እንደሚመጡ ይናገራሉ።
በተለይም እነዚህ አገራት በህዳር ወር ላይ ከፍተኛ ዝናብና አውሎ ንፋስ በቀላቀለው የሆሪኬን ማዕበል መመታታቸው የአገሬውን ዜጎች ሁኔታ አክፍቶታል።
በትናነትናው ዕለት፣ ጥር 10/2013 ዓ.ም የሜክሲኮው ፕሬዚዳንት ባደረጉት ንግግር አሜሪካ የስደተኞች ፖሊሲዋን እንድታሻሽል በጥብቅ ጠይቀዋል።
"ወቅቱ በስደተኞች ፖሊሲ ላይ የተገባው የማሻሻያ ቃል የሚተገበርበት ነው፤ እሱንም ነው ተስፋ የምናደርገው" ብለዋል።
አክለውም "በ ጆ ባይደን የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የስደተኞች ፖሊሲን ማሻሻያ እንደሚያጠናቅቁ ተመራጩ ፕሬዚዳንት ሲናገሩ ሰምቻለሁ። ተስፋም የማደርገው ይህንንኑ ያሳካሉ ብዬ ነው" ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ በተጨማሪም መንግሥታቸው ስደተኞች ወደ ሜክሲኮ እንዳይገቡ ተፅእኖ ለማድረስ እንደሚሞክር ቢናገሩም በማስከተልም የስደተኞቹ መብትም ሊከበር ይገባል የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል።
ሰኞ እለት በአብዛኛው ከሆንዱራስ የተነሱ ካራቫን ተብሎ በሚታወቀው የጅምላ ቡድን የሚጓዙ 4 ሺህ ስደተኞችን የፀጥታ ኃይሎች ለመበታተንም ሙከራ አድርገው ነበር። ስደተኞች ቫዶ ሆንዶ በምትባል አካባቢም ሰፍረዋል።
ፖሊሶቹ ስደተኞቹን ከመጠለያቸው እንዲወጡና ወደመጡበት 50 ኪሎሜትር ርቀት ወዳለው የሆንዱራስ ድንበርም እንዲመለሱ እያስፈራሩዋቸውም እንደነበር የአይን እማኞች አሳውቀዋል።
ስደተኞቹ በተወሰነ መልኩ ቢበታተኑም በርካቶቹ ግን ድንጋይ ወደ ፖሊስ በመወርወር ምላሽ ሰጥተዋል። ፖሊስም አስለቃሽ ጋዝ ረጭቷል።
ቡድኑ ከቅዳሜ ጀምሮ መንገዳቸው ቢዘጋቸውም እነሱም ዋነኛ ጎዳናዎችን በመዝጋት የትራፊክ መጨናነቅ ፈጥረዋል።
አንዳንድ ስደተኞች የከበቡባቸውን የፀጥታ ኃይሎች በኃይል ለማለፍ በሚሞክሩበት ወቅት ግጭቶች ተከስተዋል።
ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከደቡባዊ አሜሪካ ድንበር በሜክሲኮ በኩል የሚገቡ ስደተኞችን ህገወጥ በማለት ከፍተኛ ቁጥጥር እንዲደረግ አዘው ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ በሜክሲኮ፣ ጓቲማላ፣ ሆንዱራስና ኤልሳልቫዶርም አገራት ላይ የስደተኞችን እንቅስቃሴ እንዲቆጣጠሩ ከፍተኛ ጫና እያሳረፉባቸው ነበር።
ተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የትራምፕን ጥብቅ የስደተኞች ፖሊሲ አስተዳደራቸው እንደሚያሻሽል ቃል ቢገቡም፤ ፖሊሲዎች በአንድ ምሽት ስለማይቀየሩ ስደተኞች ጉዟቸውን እንዳይጀምሩ አስጠንቅቀዋል።