የኡጋንዳ ምርጫ 2021፡በኡጋንዳ ምርጫ ፕሬዚዳንት ሙሴቪኒ እየመሩ ነው ተባለ

ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኡጋንዳ ሐሙስ ጥር 6/2013 ዓ.ም ብሔራዊ ምርጫ አካሂዳለች። በዚህ ምርጫ አገሪቷን ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ የመሯት ፕሬዚዳንት ሙሴቬኒና ሙዚቀኛና ፖለቲከኛው ቦቢ ዋይን ዋነኛ ተፎካካሪ ሆነዋል።

በምርጫ ቅስቀሳውም ወቅት ከፍተኛ ሁከትን ባስተናገደችው ኡጋንዳ ከ50 ሰዎች በላይ ህይወታቸውን አጥተዋል። በምርጫው ሰሞንም ማህበራዊ ሚዲያዎችን ያገደች ሲሆን ከዋዜማውም ጀምሮ ኢንተርኔት ተቋርጧል። የምርጫ ውጤቱ በነገው ዕለት፣ ቅዳሜ የሚገለፅ ይሆናል።

  • በኡጋንዳ ምርጫ ፕሬዚዳንት ሙሴቪኒ እየመሩ ነው ተባለ

በትናንትናው ዕለት በኡጋንዳ በተደረገው ምርጫ ዩዌሪ ሙሴቪኒ የመሪነት ቦታውን ጨብጠዋል ተባለ።

በዛሬው ዕለት የምርጫ ኮሚሽኑ የመጀመሪያ ደረጃ ውጤቱ ይፋ ባደረገበትም ዕለት እስካሁን ባለው ቆጠራ የመጪውን ፕሬዚዳንትነት ቦታ ሙሴቪኒ እየመሩ መሆኑን አሳውቋል።

ፕሬዚዳንት ሙሴቪኒ 1 ሚሊዮን 536 ሺህ 205 ድምፅ (65.02 በመቶ) በማግኘት እየመሩ ሲሆን፣ ዋነኛ ተቃናቃኙ ሮበርት ክያጉላንያ በመድረክ ስሙ ቦቢ ዋይን በበኩሉ 647 ሺህ 146 ድምፅ (27.39) በማግኘት እየተከተለ መሆኑንም የምርጫ ኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል።

ውጤቱ የተሰበሰበው ከ8 ሺህ 310 የምርጫ ጣቢያዎች ነው። በአጠቃላይ በአገሪቱ 34 ሺህ 684 የምርጫ ጣቢያዎች አሉ።

ቦቢ ዋይን በበኩሉ ትናንትና በተደረገው ምርጫ ከፍተኛ ማጭበርበርና በግጭቶች የተሞላ ነው ቢልም ውንጀላውን አስመልክቶ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።

የኡጋንዳ መንግሥት በበኩሉ ምርጫው ሰላማዊ ነበር ብሏል።

  • የኡጋንዳ ምርጫ ኮሚሽን ኢንተርኔት ቢቋረጥም ውጤቱ እየተላከ መሆኑን አረጋገጠ

በትናንትናው ዕለት ብሔራዊ ምርጫዋን ባካሄደችው ኡጋንዳ ኢንተርኔት ሙሉ በሙሉ ቢዘጋም የምርጫ ውጤቶቹ ወደ ዋናው ማዕከል እየተላኩ እንደሆነ የአገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል።

የኮሚሽኑ ኃላፊ ሲሞን ብያባካማ የምርጫውን ውጤትም ለማስተላለፍ ሌሎች ውስጣዊ መንገዶችን እየተጠቀሙ እንደሆነ ቢናገሩም ዝርዝር ከመስጠት ተቆጥበዋል፥

"የምርጫውን ውጤት ለመላክ ኢንተርኔት እየተጠቀምን አይደለም። የራሳችንን ስርአት እየተጠቀም ነው። አትጨነቁ፣ ኢንተርኔቱ ቢቋረጥም ውጤቱ መድረሱ አይቀርም፤ ይፋም ይሆናል" በማለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ዛሬ ጥዋትም ኮሚሽኑ ከ330 የምርጫ ጣቢያዎች ድምፅ ሰበሰብኩት ባለው መረጃ መስረት የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት ያሳወቀ ሲሆን በዚህም መሰረት አገሪቷን ከሶስት አስርት አመታት በላይ የመሯት ዩዌሪ ሙሴቪኒ እየመሩ ነው ማለቱንም ደይሊ ሞኒተር ጋዜጣ አስነብቧል።

አገሪቷ በአጠቃላይ 34 ሺህ 684 የምርጫ ጣቢያዎች አሏት።

በኡጋንዳ ህግ መስረት ምርጫው በተካሄደ በ48 ሰዓታት ውስጥ የምርጫው ኮሚሽን ከሁሉም ግዛቶች ድምፆችን ሰብስቦ ውጤቱን ማሳወቅ አለበት።

የፓርላማ መቀመጫ ያሸነፉ አባላት በተለያዩ ግዛቶች በሚገኙ ማዕከላት ዝርዝራቸው የሚገለፅ ሲሆን በሌላ በኩል የፕሬዚዳንትነቱ አሸናፊ በመዲናዋ ካምፓላ በሚገኘው ማዕከል ይፋ ይሆናል።

ሮበርት ክያጉላንይ ወይም በመድረክ ስሙ ቦቢ ዋይን ተብሎ የሚታወቀው ሙዚቀኛና ፖለቲከኛ የፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ዋነኛ ተቀናቃኝም ሆኖ ወጥቷል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ባለስልጣናቱ የትኛውንም ማህበራዊ ሚዲያዎች እንዲሁም ቪፒኤኖችም እንዲዘጉ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ቀጣይ ሐሙስ በሚካሄደው የኡጋንዳ ምርጫ ልናውቃቸው የሚገቡ 5 ጉዳዮች