ኡጋንዳ ከሙዚቀኛው ተቃዋሚ ጋር ግንኙነት ያላቸው የዩቲዩብ ቻናሎች እንዲታገዱ ጠየቀች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የኡጋንዳ መንግሥት ከታዋቂው ሙዚቀኛና ተቃዋሚ ቦቢ ዋይን ግንኙነት ያላቸው የዩቲዩብ ቻናሎች እንዲታገዱ ጠይቋል።
በኡጋንዳ የኮሚዩኒኬሽን ዘርፉን በዋነኝነት የሚቆጣጠረው አካል አስራ አራት የዩቲየብ ቻናሎች እንዲዘጉ ጠይቋል።
ተቆጣጣሪው አካል ደብዳቤውን የፃፈው የዩቲዩብ ባለቤት ለሆነው ጉግል ሲሆን በባለፈው ወር ከደረስው ነውጥም ጋር ግንኙነት ያላቸውና ለ50 ሰዎችም መሞት ተጠያቂ ናቸው ያላቸው እንደሆነም አስፍሯል።
በአገሪቱ ውስጥ ዋነኛ ተቃዋሚ የሚባለው ሮበርት ካያጉላንይ ወይም ቦቢ ዋይን እስር ተከትሎም በመዲናዋም ካምፓላም ሆነ በዋነኞቹ ከተሞች ነውጥ ተከስቷል።
ሙዚቀኛው ቦቢ ዋይን የኮሮናቫይረስ መመሪያዎችን ጥሷል በሚልም ነው ለእስር የተዳረገው።
እንዲታገዱ የተወሰኑት የዩቲዩብ ቻናሎች ከሙዚቀኛው ጋር ግንኙነት አላቸው ቢባልም የኡጋንዳ ኮሚዩኒኬሽን የህግ ጉዳዮች ኃላፊ በበኩላቸው "የአጋጣሚ ጉዳይ ነው" ማለታቸውን ብሉምበርግ ዘግቧል።
ኮሚሽኑ ለጉግል በፃፈው ደብዳቤ የዩቲብ ቻናሎቹን ነውጡን ለማነሳሳት ተጠቅመውበታል፤ ከህግ ውጭ ያላቸውንም ይዘቶች አሳይተዋል በማለትም ዴይሊ ሞኒተር ጋዜጣ ፅፏል።
ኡጋንዳ በጥር ወር ምርጫዋን ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ናት። አገሪቷን ከሶስት አስርት አመታት በላይ የመሯት ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪንም በምርጫው ይወዳደራሉ።












