ፑቲን ለጆ ባይደን የዘገየ የእንኳን ደስ አለዎት መልእክት አስተላለፉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ቭላድሚር ፑቲን ለጆ ባይደን የዘገየ የእንኳን ደስ አለዎት መልእክት አስተላለፉ
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከዓለም መሪዎች በጣም ዘግይተው ለተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የእንኳን ደስ አለዎት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በሩሲያ የፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት፣ ክሬምሊን፣ የኅዳሩ ምርጫ አሸናፊው በውል እስኪለይ ድረስ ዝምታን እንደሚመርጥ አስቀድሞ ገልጾ ነበር፡፡
አሁን ፑቲን እንኳን ደስ አለዎ የሚለውን መልእክት ያስተላለፉት የግዛት ድምጽ ተወካዮች (ኤሌክቶራል ኮሌጅ አባላት) ተሰብስበው የጆ ባይደንን አሸናፊነት ትናንት ማወጃቸውን ተከትሎ ነው፡፡
ባይደን ከ50 ግዛቶች 306 የወኪል ድምጽ ሲያገኙ ትራምፕ ግን 232 ላይ መቆማቸው ይታወሳል፡፡ በአሜሪካ የምርጫ አሰራር 270 እና ከዚያ በላይ የወኪል ድምጽ ያገኘ እጩ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ተብሎ ይጠራል፡፡
ያም ሆኖ ዶናልድ ትራምፕ እስከዛሬም ተሸናፊነታቸውን በይፋ አልተቀበሉም፡፡ ከወዳጆቻቸው ጭምር መሸነፋቸውን ጨክነው እንዲቀበሉ ውትወታው ቢበረታባቸውም ሽንፈት ሞት ሆኖባቸዋል፡፡
በአሜሪካ ሴኔት አብላጫ ወንበር መሪ ተወካይ ሪፐብሊካኑ ሚች ማኮኔል ለመጀመርያ ጊዜ ባይደንን እንኳን ደስ አለዎት ማለታቸው ዛሬ ተዘግቧል፡፡
እኚህ የትራምፕ ወዳጅ ዝምታውን መስበራቸው ትራምፕ ባይደንን የማቆም ዕድላቸው ስለመሟጠጡ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል በዋና ዋና ግዛቶች ላይ እሳት የላሱ ጠበቆቻቸውን በማዝመት የክስ ዶሴ ማስከፈታቸው አይረሳም፡፡
ትራምፕ የሽንፈትን ጽዋ ለመቅመስ አሻፈረኝ ይበሉ እንጂ የአሜሪካ ምርጫ በተደረገ በሳምንት ውስጥ አብዛዎቹ የዓለም መሪዎች ለጆ ባይደን የመልካም ምኞች መግለጫ ልከዋል፡፡ ቭላድሚር ፑቲን ግን ይህ እንዲዘገይ አድርገዋል፡፡
ባይደንና ፑቲን ኦባማ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከነበሩበት ዘመን ጀምሮ ግንኙነታቸው የሻከረ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ተመራጩን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ዘግይተው ‹ሹመት ያዳብር› ለማለት ከፑቲን ሌላ የሜክሲኮው ፕሬዝዳንት ሎፔዝ ኦብራዶር ይጠቀሳሉ፡፡
ውዝግብ የማያጣቸው የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ዣዪር ቦልሶናሮን እንዲሁ ለጆሴፍ ባይደን መልካም ምኞት ለመግለጽ የዘገዩ መሪ ሆነዋል፡፡
እነዚህ ሦስቱ መሪዎች ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በአገር ደረጃ ብቻም ሳይሆን በግልም ጠበቅ ያለ ግንኙነት የነበራቸው በመሆናቸው ምናልባት ቀደም ብለው ለጆ ባይደን መልካም ምኞች ቢያስተላልፉ ትራምፕን ማስቀየም ይሆንብናል ብለው ሰግተው የቆዩ እንደሆኑ ተገምቷል፡፡
ክሬምሊን ባወጣው የመልካም ምኞች መግለጫ ፑቲን ከአዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ ስለመሆናቸው ገልጾ ለባይደን መልካም የሥራ ዘመንን ይመኛል፡፡
‹‹በተለይ ሩሲያና አሜሪካ የዓለምን ደኅንነትና ሰላምን ለመጠበቅ ልዩ ኃላፊነት ያለባቸው አገራት እንደመሆናቸው ልዩነታቸው እንዳለ ሆኖ ብዙ ችግሮችን በመቀራረብ መፍታት እንደሚችሉ እናምናለን›› ይላል የመልካም ምኞቹ ሙሉ ቃል፣ አንድ አንቀጽ፡፡
ጆ ባይደን ትራምፕ አቅብጠዋቸዋል በሚባሉት ፑቲን ላይ ጠበቅ ያለ የዲፕሎማሲና የንግድ እቀባ እርምጃዎችን ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እስከ አሁን ለጆ ባይደን እንኳን ደስ አለዎ የሚል መልእክት ያላስተላለፉት መሪ የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆንግ ኡን ናቸው፡፡












