የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ፅህፈት ቤት ሀላፊ ማርክ ሚዶውስ በኮሮና ተያዙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ፅህፈት ቤት ሀላፊ ማርክ ሚዶውስ የኮቪድ-19 ምርመራ አድርገው ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ባለስልጣናት ለአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ገለጹ፡፡
የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ዝግጅቶች ላይ ብዙ ጊዜ የሚታዩት ሚዶውስ እንዴት ቫይረሱ እንደያዛቸው ግልጽ አልሆነም፡፡
ኃላፊው በትራምፕ አስተዳደር ውስጥ ከሚሠሩ እና በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች መካከል አንደሱ ሲሆኑ በአሜሪካ 230,ሺህ የሚሆኑ ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው አልፏል፡፡
አሜሪካ አርብ ከ127 ሺህ በላይ አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ያስመዘገበች ሲሆን ይህም ለሦስተኛ ተከታታይ ቀናት ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቁልፍ ርዕስ የነበረ ሲሆን ሰዎች ድምጻቸውን በፖስታ እና ቀደም ብለው በአካል እንዲሰጡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
ከቀናት በፊት ሚዶውስ ከሲኤንኤን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አሜሪካ "ወረርሽኙን ለመቆጣጠር አትችልም" ያሉ ሲሆን ኮቪድ-19 ማሸነፍ የሚቻለው በክትባት እና ህክምና ብቻ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ኃላፊው ቫይረሱ መጀመሪያ መቼ እንደተገኘባቸው ወይም የበሽታውን ምልክቶች ስለማሳየታቸው ግልጽ አልሆነም፡፡ እሳቸውም እስካሁን አስተያየት አልሰጠም፡፡
ሜዶውስ በምርጫ ዘመቻው የመጨረሻ ቀናት ከፕሬዚዳንቱ ጋር የተጓዙ ሲሆን በኋይት ሃውስ በደርዘን የሚቆጠሩ የትራምፕ ደጋፊዎች በተገኙበት የምርጫ ምሽት ግብዣ ላይም ነበሩ፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ፣ ባለቤታቸው ሜላኒያ እና ልጃቸው ባሮን ከኮቪድ-19 ተገኝቶባቸው እንዳገገሙ ይታወሳል። የብሄራዊ ደህንነት አማካሪው ሮበርት ኦብሪየን፣ ከፍተኛ አማካሪው ስቲፈን ሚለር እና የኋይት ሃውስ አማካሪ ሆፕ ሂክስም በተመሳሳይ ከቫይረሱ አገግመዋል፡፡












