የአሜሪካ ምርጫ፡ ቆጠራው በቀጠለበት ምርጫ ባይደን እንደሚያሸንፉ ተንብየዋል

ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የማክሰኞውን የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተከትሎ ዶናልድ ትራምን ለማሸነፍ ከጫፍ የደረሱት ጆ ባይደን እንደሚያሸንፉ በመተማመን በድጋሚ ተናግረዋል ፡፡

የዴሞክራቲክ ፓርቲው ዕጩ ኋይት ሐውስ ለመግባት ከሚያስፈልጉት 270 የኤሌክቶራል ኮሌጅ ድምፆች 253ት ያህሉ አግኝተዋል፡፡

በተጨማሪም ባይደን ወሳኝ ግዛቶች በሆኑት በጆርጂያ፣ ኔቫዳ፣ ፔንሲልቬንያ እና አሪዞና እየመሩ ነው፡፡

የባይደን ድል ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከአራት ዓመት በኋላ በመጪው ጥር ስልጣናቸውን እንዲለቁ ያደርጋቸዋል፡፡

ባይደን ምን አሉ?

ባይደን አርብ ምሽት ዊልሚንግተን ደላዌር ለነበሩ ደጋፊዎቻቸው ሲናገሩ "ይህንን ውድድር እናሸንፋለን" ብለዋል፡፡ መድረኩ ላይ የባይደን ምክትል በመሆን የሚወዳደሩት የካሊፎርኒያ ሴናተር ካማላ ሃሪስ ተገኝተዋል፡፡

ከ 300 በላይ የኤሌክቶራል ኮሌጅ ድምጾችን ለማሸነፍ በትክክለኛው መንገድ ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል። በታሪክ ውስጥ ከማንኛውም የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ በላይ በምርጫ ከ74 ሚሊዮን በላይ በሆኑ ሰዎች ተመርጠዋል፡፡

አሜሪካውያን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን፣ የተዳከመውን ኢኮኖሚ፣ የአየር ንብረት ለውጥን እና ዘረኝነትን እንዲዋጉ ስልጣን እንደተሰጣቸው ባይደን ተናግረዋል፡፡

የሪፐብሊካኑን ዶናልድ ትራምፕን ያልጠቀሱት ባይደን "እኛ ተቃዋሚዎች ልንሆን እንችላለን ግን ጠላቶች አይደለንም እኛ አሜሪካውያን ነን" ብለዋል፡፡

ባይደን የማሸንፊያ ንግግራቸውን እንደሚያቀርቡ የታቀደ ቢሆንም በምርጫው ውጤት ላይ የመገናኛ ብዙሃን አሸናፊ መሆናቸውን አለመጥቀሳቸውን ተከትሎ አጠቃላይ መረጃ ለመስጠት መርጠዋል።

ዴሞክራቱ በድጋሚ ለአሜሪካኖች ንግግር እንደሚያደርጉ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ለዋይት ሀውስ በአውሮፓውያኑ 1988 እና በ2008 የተወዳደሩት ባይደን በ78 ዓመታቸው ከተመረጡ አንጋፋው ፕሬዝዳንት ይሆናሉ፡፡

በዚህ ሳምንት መጨረሻ አሸናፊ እንደሆኑ ከተነገረ ሰኞ የሽግግር ሂደቱ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የአሜሪካው የደህንነት አገልግሎት የባይደንን ደህንነት ለማጠናከር አንድ ቡድን ወደ ደላዌር ማጠናከሪያ ልኳል፡፡ የፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር በዊልሚንግተን አየር ክልል ላይ በረራዎችን አግዷል፡፡

ትራምፕ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሽንፈታቸውን እንደሚቀበሉ የሚያሳይ ምንም ፍንጭ የለም፡፡

ትራምፕ አርብ ከሰዓት በኋላ በትዊተር ገጻቸው ላይ "ጆ ባይደን የፕሬዚዳንቱን ቢሮ እንዳገኘ ተሳስቶ መግለጽ የለበትም። እኔም ያንን ማድረግ እችል ነበር፡፡ የህግ ሂደቶች አሁን በመጀመር ላይ ናቸው!" ብለዋል።

ትራምፕ በምርጫ መጭበርበር ላይ ማስረጃ የሌላቸውን ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

በኋይት ሀውስ ውስጥ ያለው መንፈስ ምን ይመስላል?

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ብዙ አጋሮቻቸው በቴሌቪዥንም ሆነ በጎዳናዎች ላይ ደግፈዋቸው አለመቆማቸው ተቆጥተዋል፣ ቅር ተሰኝተዋልም ሲሉ የዋይት ሃውስ ባለስልጣናት አርብ አስታውቀዋል።

ትራምፕ ቴሌቪዥን እየተመለከቱ፣ ለምርጫ የዘመቻ ቢሮዎች የስልክ ጥሪ በማድረግ ጊዜያቸውን በ'ኦቫል' ቢሮ እና በመኖሪያ ቤታቸው መካከል ሲያሳልፉ ቆይተዋል፡፡

በርካታ ረዳቶቻቸው ሥራ ላይ አልተገኙም። ዋይት ሀውስም "ባዶ" እና የሃዘን ድባብ ያጠላበት ነው ተብሏል፡፡

ዜናውን ይበልጥ አሳዛኝ የሚያደርገው አርብ ማታ የ 61 አመቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ፅህፈት ቤት ሀላፊ ማርክ ሚዶውስ በኮሮናቫይረስ በሽታ መያዛቸው ሪፖርት መደረጉ ነው።

ይህ የሆነው አሜሪካ በቀን ክብረ ወሰን የሆነ ከ125 ሺህ በላይ አዲስ ኮሮናቫይረስ ያለባቸውን ሰዎች ባስመዘገበችበት ዕለት ነው፡፡

ፕሬዚዳንቱ ለከፍተኛ አማካሪዎቻቸው በውጤቱ ላይ የሕግ ጥያቄዎች እንደሚቀጥሉ ቢያመለክቱም ለእንዲህ ዓይነቱ ሙግት የሚሆን ጠንካራ መረጃ አልቀረበም።