የአየር ጥቃት ስለሚኖር ነዋሪዎች በከተሞች እንዳይሰበሰቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስጠነቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Screen grab
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ መንግሥት በትግራይ ክልል ላይ እየወሰደ ባለው እርምጃ የአየር ጥቃቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት ጥቅምት 27/2013 ዓ.ም በብሄራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው በትግርኛ ለትግራይ ህዝብ ባስተላለፉት መልዕክት የአየር ጥቃቱ ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ያደረገ እንዳልሆነና "አደገኛ" ብለው የጠሩትን ኃይል የያዛቸውን ቦታዎች ኢላማ ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
"በዚህም ሁኔታ ያልታሰበ አደጋ እንዳይመጣ ነዋሪዎች በከተማ አካባቢ ተሰብስባችሁ መንቀሳቀስ እንድትቀንሱ አሳስባለሁ" በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል አስተዳደር ህወሃት ላይ የከፈተውን ጦርነት "ህገ መንግሥቱን የማስከበር ሂደት ነው" ካሉም በኋላ"ተገደን የገባንበት ጦርነት ነው" ብለዋል።
"የተከበርከው ህዝብ መከላከያ ተኝቶ እያለ አጥቅተዋል። ዓለም እያየ ጥቃት ፈፅመዋል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በአጠቃላይ የህወሃትን አባላት ሳይሆን "ሁሉም ህወሃት አይደለም ጠላታችን። ጠላታችን በህወሃት ውስጥ ያለ ሃይል ነው" ሲሉ አክለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጀምሮ አገርን ሰላም ለማድረግና ብልፅግና ለማምጣት ሲሰሩ መቆያታቸውን ጠቅሰው በዚህ ወቅት ግን "ህወሐት ውስጥ ያለው ከሃዲ ሃይል ጉዟችንን ሲያደናቅፍ ቆይቷል። ልማት ሲያደናቅፍ ነበር፤ ይህ ሃይል የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ ህዝብ ተነጥሎ የሰላምና ብልጽግና ተካፋይ እንዳትሆን አድርጎሃል" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የትግራይ ህዝብ በሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲጠላ በስሙ ብዙ መጥፎ ነገሮች ተሰርቷል ያሉ ሲሆን፤ ህገ መንግስትም ጥሷል ሲሉ ከሰውታል።
ህወሐት ህገ መንግስት ጥሷል ያሉባቸውን አምስት ምክንያቶች ያነሱ ሲሆን፦
- በፓርላማ የወጡ ህጎችን ውሳኔ መንፈግ
- ከህግ ውጪ ከአለም አቀፍ ተቋማትና ሃገራት በጎን ግንኙነት መጀመር
- በመላው አለምና አገራችን በተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ፌደሬሽን ምክር ቤት ምርጫ እንዲራዘም የወሰነውን ውሳኔ ጥሶ ህጋዊ ያልሆነ ምርጫ ማካሄድ
- ለፌደራልና ክልል መንግስታት እውቅና ባለመስጠት ግንኙነት ማቋረጥ
- በሌሎች ክልሎች ከሚገኙ የጥፋት ሃይሎች ጋር በመጣመር ግጭቶችን መፍጠርና የንጹሃን ዜጎች ህይወት እያጠፋ ነው የሚሉ ጉዳዮች አንስተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ግጭቱን ተከትሎ የተቋረጠው የመብራትና የስልክ አገልግሎትም በክልሉ አስተዳዳሪ እንደተፈፀመ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመከላከያ ሰራዊትም ጋር ህዝቡ እንዲተባባርና ወደ ልማት ስራው እንዲገባ ለትግራይ ህዝብ ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) በበኩላቸው የመብራትና የስልክ አገልግሎት የተቋረጠው በፌደራል መንግሥቱ እንደሆነ በትናንትናው ዕለት፣ ጥቅምት 26/2013 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ የመጣው የፌደራልና የትግራይ ክልል መንግሥት ግንኙነት የማይታረቅ ደረጃ ደርሶ ከቀናት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ህወሃት በትግራይ የሚገኘው የመከላካያ ካምፕ ላይ ጥቃት ማድረሱን ገልፀው ጦርነት መከፈቱን አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው የመከላከያ ሠራዊት በኮማንድ ፖስት እየተመራ "ሀገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትእዛዝ ተሰጥቶታል" ብለዋል።
የትግራይ ክልል በበኩሉ በክልሉ የሚገኙት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰሜን ዕዝ ሰራዊት አባላትና አዛዦች ከትግራይ ክልል መንግሥት ጎን ለመሰለፍ ወስነዋል ብሏል።












