የእስራኤል እና የአረብ አገራት እርቅ የጦር መሣሪያ ገበያውን ይለውጣል?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለመካከለኛው ምሥራቅ ፀሐይ ወጣ ሲሉ ተደምጠዋል።
እስራኤል ከሦስት የአረብ አገራት ጋር የሰላም ስምምነት ለማድረግ ወስናለች። ይህ ታሪካዊ ውሳኔ በርካታ ጉዳዮች ላይ ለውጥ ያመጣል።
እስራኤል መጀመሪያ ላይ ሰላም ያወረደችው ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ጋር ነው።
አገሪቱ ከአሜሪካ ተዋጊ ጀቶች ለመግዛት በዝግጅት ላይ ነበረች። የቀጠናው ዘመነኛ የጦር መሣሪያ ባለቤት የሆነችው እስራኤል የተሻለ መሣሪያ ልታቀርብ ትችላለች።
የቀጠናው አገሮች መሣሪያ ከእስራኤል መግዛት ከጀመሩ፤ ኢራን እንደምትጎዳ የምታምነው አሜሪካ ተጠቃሚ ትሆናለች ማለት ነው። አሜሪካ ኢራንን ከተቀረው ዓለም የመነጠል ግብ አላት።
የጦር መሣሪያ ሽያጭ
ኤፍ-35 ላይትኒንግ በአሜሪካ መከላከያ የተሠራ የጦር አውሮፕላን ነው። በመላው ዓለም ካሉ መሣሪያዎች የላቀ ቦታ ይሰጠዋል።
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ይህን መሣሪያ ለመግዛት ለስድስት ዓመታት ጠብቃለች።
ከተሳካላት መሣሪያው ያላት የመጀመሪያዋ የአረብ አገር ትሆናለች
በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኝ ተቋም ውስጥ የሚሠሩት ጀስቲን ብሮንክ፤ “ኤፍ-35 በሚቀጥሉት 20 ዓመታት እስካሁን በአየር ኃይል ታሪክ ያልታየ መሣሪያ ይሆናል። የመሣሪያው ባለቤት መሆን ያስከብራል” ይላሉ።
ባለፈው ሳምንት ትራምፕ 50 ኤፍ-35፣ በ10.4 ቢሊዮን ዶላር ለዩናይትድ አረብ ኤምሬቶች የመሸጥ እቅድ እንዳላቸው ለምክር ቤት መግለጻቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ለእስራኤል በቀጠናው አገሮች እውቅና ማግኘት ታሪካዊ ነው።
ኤምሬቶች ደግሞ ለምጣኔ ሀብት እድገትና በቀጠናው ኃያል ለመሆን ይረዳታል። በሌላ በኩል የአረቡ አገራትን ውሳኔ ፍልስጤም “ክህደት ነው” ብላለች።
ፍልስጤም ራሷን የቻለች አገር መሆኗን በተመለከተ የአረቡ አገራትን ድጋፍ ትፈልጋለች። ኤምሬቶች አሜሪካ ሠራሹን ኤምኪው-9 ሰው አልባ አውሮፕላን ለመግዛት ለዓመታት ሞክራለች።
ነገር ግን የጦር መሣሪያ የውጪ ንግድን በተመለከተ የወጣው ስምምነት አግዷት ቆይቷል።
የቻይናን የሰው አልባ አውሮፕላን ሽያጭ መቀልበስ የሚፈልጉት ትራምፕ መሣሪያውን የሚሸጡበት መንገድ ሲያፈላልጉ ነበር።
የእስራኤል መሪዎች ጥያቄ
በእስራኤል አስተዳደር ካሉ ጥቂቱ ለአረብ ኤምሬቶች ኤፍ-35 መሸጡን አይደግፉም። እስራኤል በቀጠናው ያላትን ወታደራዊ የበላይነት ያሳጣታል ብለው ይሰጋሉ።
በአሜሪካ ሕግ መሠረት ለመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የሚሸጥ መሣሪያ እስራኤል በቀጠናው ያላትን ስፍራ መገዳደር የለበትም።
እስራኤል የቀጠናው ብቸኛ የኤፍ-35 ባለቤት የሆነችውም በዚህ መርህ መሠረት ነው።
የእስራኤል አየር ኃይል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2018 ላይ ኤፍ-35ን ለውጊያ የተጠቀመ የመጀመሪያ ሠራዊት መሆኑን ገልጿል። ይህም በሶርያ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነው ሊሆን የሚችለው።
የእስራኤል ኤፍ-35 በሊባኖስ መዲና ቤሩት ሰማይ ሲበር የሚያሳይ ፎቶ ውዝግብ አስነስቶ ነበር።
ከዛም የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ኤፍ-35 ለዩናይትድ አረብ ኤምሬቶች እንዲሸጥ በሚስጥር መስማማታቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙሀን ዘገቡ።
የጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ ዘገባውን አጣጥሏል።
የኔታንያሁ ተቀናቃኙ የመከላከያ ሚንስትር ቤኒ ጋንዝ ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ዋሽንግተን አቅንተው ነበር።
እስራኤል ቪ-22፣ ኤፍ-15 ተዋጊ ጀት እንዲሁም ሌሎች እንዲሸጡላት የሚፈልጓቸውን መሣሪያዎች ዝርዝር ይዘው መጓዛቸው ተዘግቧል።
“ለገልፍ አገሮች መሣሪያ መሸጥ ድርጊታቸውን መደገፍ ነው” ዋሽንግተን ውስጥ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ዙርያ የሚሠሩት ዊልያም ሀርተግ፤ “አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ የጦር መሣሪያ ንግድ ከራሷ ጋር እየተሽቀዳደመች ነው” ይላሉ።
ሳዑዲ አረቢያ፣ ባህሬን እና ሱዳን ከእስራኤል ጋር ሰላም ካወረዱ ከአሜሪካ የጦር መሣሪያ የመግዛት እድላቸው ይሰፋል።
“ለገልፍ አገሮች መሣሪያ መሸጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰታቸውን ጨምሮ ሌላም ድርጊታቸውን መደገፍ ነው” ሲሉ ያስረዳሉ።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የኢራን ጉዳይ እንደሚያሳስባቸውም ይናገራሉ። ኢራን በሁቲ አማጽያን እና በመንግሥት ደጋፊዎች እንዲሁም ሳዑዲ በምትደግፈው ኃይል ግጭት እየተናጠች ነው።
ሰንአ ውስጥ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ያቋቋሙት ራድያ አልሙታክወል “በቀጠናው መሣሪያ መሸጥ ድርጊቱን ግፉበት ማለት ነው። ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት ያደረሱ ከ500 በላይ የአየር ጥቃቶች መዝግበናል። አብዛኞቹ መሣሪያዎች የተሠሩት አሜሪካ የተቀሩት ደግሞ ዩኬ እና ጣልያን ሠራሽ ናቸው” ይላሉ።
የወታደራዊ ጉዳይ ተንታኙ ጀስቲን ብሮንክ እንደሚናገሩት፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፤ የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን የመን ላይ መጠቀም ትፈልጋለች።
የመንን የሰው አልባ አውሮፕላን ውጊያ “መሞከሪያ” እንዳደጓትም ያስረዳሉ።
ኢራንን የሚደግፉት ወገኖች
ለዩናይትድ አረብ ኤምሬቶች ኤፍ-35 ከተሸጠ ሌሎች የአረብ አገሮችም ሊከተሉ ይችላሉ።
አሜሪካ የጦር መሣሪያዎቹን ለገልፍ አገሮች በመሸጥ ገበያዋን የማሳደግ እቅድ አላት።
ትራምፕ የአስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌን ተጠቅመው ከምክር ቤቱ የሚገጥማቸውን ተቃውሞ በማለፍ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር የሚያወጡ መሣሪያዎችን ለሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ጆርዳን ሸጠዋል።
በእስራኤል የአሜሪካ አምባሳደር ዴቪድ ፊደርማን ኤምሬቶች የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ኤፍ-35 ሊያገኙ ይችላሉ የሚለውን ስጋት አጣጥለው ነበር።
እስራኤል ወታደራዊ የበላይነቷን እንደማታጣ እና እንዲያው ጠንካራ አጋሮች በቀጠናው ልታገኝ እንደምትችል ለጀሩሳሌም ፖስት ተናግረው ነበር።
ተንታኞች የኢራን አየር ኃይል እድሜው ቢገፋም አቅሙ እያደገ እንደመጣ ይናገራሉ።
ባለፉት አሠርታት ቴህራን የባለስቲክ ሚሳኤልን ጨምሮ በተለያየ ዘርፍ ኃይሏን ስታጠናክር ቆይታለች ሲሉ የአሜሪካ አየር ኃይሉ ሌ/ኮለኔል ክርስትን ማክቪን ይናገራሉ።
የሰላም ስምምነቱ ኤምሬቶች ኤፍ-35 የመግዛት ጥያቄያቸውን ያፋጥነዋል? የሚለው ላይ የተለያየ ሐሳብ አለ።
ምክር ቤቱ ሊያጓትተው ወይም ሊገታው ይችላል። ጆ ባይደን ፕሬዘዳንት ሆነው ከተመረጡ ነገሮች ሊለዋወጡም ይችላሉ።












