የአሜሪካ ምርጫ፡ መምረጥ እንደሚችሉ ያልታወቁት 750 ሺዎቹ የአሜሪካ ታራሚዎች

ከእስር በኋላ ሌላ እድል በህይወት ላይ ይኖር ይሆን?

ከሶስት አስር አመታት በላይ በእስር የቆየው ሬናልዶ ሁድሰን በማረሚያ ቤት ህይወቱን ቀይሮ፣ የነገን ተስፋ ሰንቆ ነበር የወጣው።

ገና በታዳጊነቱ ከፍተኛ ጥቃት ያስተናገደው ሬናልዶ በነፍስ ግድያ ወንጀል ክስ ነው 37 በእስር የቆየው። በአስራዎቹ እድሜውም አደንዛዥ እፅን ይጠቀም የነበረ ሲሆን በዚህም ወቅት ነው ለእስር የተዳረገው።

መላ ህይወቱን በእስር ያሳለፈው ሬናልዶ በማረሚያ ቤትም ውስጥ እያለ ታራሚዎችን በማስተማርም ያግዝም ነበር፤ ከውጭው ካለው አለምም ጋር በምን መንገድ ግንኙነታቸውን መቀጠል ይችላሉ የሚለውም ዋናው ትኩረቱ ነበር።

የ56 አመቱ ሬናልዶ በዚህ አመት በተለይም በዚህ ወቅት ሚሊዮኖች መምረጥ አለባቸውም እያለ ነው።

ምርጫ ለምን? በእስር ቤት ያሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን መምረጥ እንደሚችሉም ሆነ እንደማይችሉ ግንዛቤው የሌላቸው ሲሆን ይህም በዲሞክራሲያዊ ሂደት ተሳታፊ እንዳይሆኑና ማህበረሰቦቻቸውን ተፅእኖ ከሚያመጡ ፖሊሲዎችም እንዲገለሉ ሆነዋል።

ሬናልዶም ከ750 ሺህ በላይ ታራሚዎችን የሚገለሉበትን መዋቅራዊ ስርአትም ከሚታገሉት አንዱ ነው።

በአሜሪካ ምርጫ ህግ መሰረት ከበድ ያለ ወንጀል የፈፀሙና ረዘም ያለ የእስር ጊዜ የተፈረደባቸው ታራሚዎች በአብዛኛዎቹ ግዛት መምረጥ አይችሉም። መምረጥ የሚችሉት በሜይን፣ ቬርሞንትና ዋሽንግተን ዲሲ ብቻ ነው።

ነገር ግን የፍርድ ጊዜያቸውን እየተጠባበቁ ያሉ፣ ወይም ቀለል ባሉ ወንጀሎች አጠር ላለ ጊዜ በእስር ያሉ ታራሚዎች መምረጥ ይችላሉ።

በአሜሪካም ውስጥ ባሉ እስር ቤቶች ውስጥ ክስ ያልተመሰረተባቸው ነገር ግን የተጠየቁትን 500 ዶላር የዋስ ገንዘብ መክፈል ባለመቻላቸው በእስር ላይ ያሉ በርካቶች ናቸው።

በቅርብ አመታት ውስጥ የዲሞክራሲ ደጋፊ ቡድኖች በጎ ፈቃደኞችን በተለያዩ የአሜሪካ እስር ቤቶች ውስጥ በመላክ መሰረታዊ ህገ መንግሥታዊ መብታቸውን እያስተማሩ ይገኛሉ።

በሂውስተን የሚገኘው የሃሪስ ማረሚያ ቤት አንድ ሺህ የሚሆኑ መምረጥ የሚችሉ ታራሚዎች መዝግበዋል።

ሳንዲያጎ ባሉ እስር ቤቶች ደግሞ በጥቁር ሙስሊሞች የሚመራና ለፍትህ የሚታገል ቡድን በእስር ቤት ያሉ ታራሚዎችን 17 ዶላር በሰዓት በመክፈል ድምፅ ለማሰባሰብም እየሞከሩ ነው።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያትም በርካታ ተሟጋቾች በየማረሚያ ቤቱ በመሄድ መምረጥ የሚችሉ እስረኞችን ስለ መብታቸው ማሳወቅ ተስኗቸዋል ተብሏል።

ስፕሬድ ዘ ቮት የሚባል ተሟጋች ቡድንም በበኩሉ ታራሚዎች በፖስታ እንዲመርጡ ለማድረግም አንድ ፕሮግራምም ጀምሯል። ይህም ፕሮግራም በ20 ግዛቶች የሚገኙ 52 እስር ቤቶችን የሚሸፍን ነው።

የቡድኑ መስራች ካት ካልቪን እንደሚናገሩት ይህንን ፕሮግራም በመጠቀም በርካታ ታራሚዎች መምረጥ መጀመራቸውን ነው።

ከፕሬዚዳንታዊው ምርጫ፣ ጥቅምት 24/ 2013 ዓ.ም በፊትም የሚሰሩባቸው እስር ቤቶች ታራሚዎች በፖስታ ድምፃቸውን እንዲልኩ እየሰሩ ነው።

ሆኖም የመራጮች መብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ከእስር ቤት ምርጫን በፖስታ መምረጥ ቀላል እንዳልሆነ ነው።

ቺካጎ ቮትስ የተሰኛ ለትርፍ ያልቆመ ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር ጄን ዲን እንደሚሉት ወረቀቶቹን ሲሞሉ በርካታ ስህተቶች እየተፈፀሙ መሆናቸውን ነው።

ከእስር ቤት ውጭ ያሉ በፖስታ የሚመርጡ ሰዎች ለምርጫ ከመመዝገብ ጀምሮ፣ ለምርጫ ቦርዱ መላክ፣ መርጦ መላክ የመሳሰሉ የተወሳሰቡ ሂደቶች ያጋጥማቸዋል። በዚህም ሁኔታ በማረሚያ ቤቶች የአቅርቦትና የገንዘብ ችግርም አጋጥሟል ተብሏል፥።

ቺካጎ ቮትስ በአንድ ጊዜ 5 ሺህ እስረኞችን መያዝ ከሚችለው ሲቲ ኩክ እስር ቤት ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያለው ሲሆን ከ2017 ጀምሮም 5 ሺህ ታራሚዎች ድምፃቸውን እንዲሰጡ ለማስቻልም መመዝገብ ችሏል።

ከዚህም በተጨማሪ በዚህ እስር ቤት የሚገኙ ታራሚዎችም አሜሪካ በዘንድሮው በምታካሂደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን በአካል ድምፃቸውን መስጠት እንዲያስችላቸው አዋጁ እንዲቀየር ግፊት አድርጓል።

ታራሚዎች ባሉበት መምረጥ የሚያስችላቸው ማሽንም በእስር ቤቱ ተገጥሞም በተሳካ ሁኔታ መምረጣቸውንም ዲን ይናገራሉ።

ሆኖም ሁሉም እስር ቤቶች እንደ ኩክ እስር ቤት ከተሟጋቾች ጋር በመቀናጀት አይሰሩም።

በማረሚያ ቤቶችም የሚያጋጥሙ እክሎች በርካታ ናቸው።

በርካታ ግዛቶች በመራጭነት ለመመዝገብ ብሔራዊ መታወቂያና ቋሚ አድራሻ ይፈልጋሉ። ነገር ግን በርካታ እስር ቤቶች ታራሚዎች ገና ሲገቡ መታወቂያቸውንም ሆነ የመንጃ ፈቃዳቸውን ይነጥቋቸዋል።

ብዙዎቹ ታራሚዎች ቋሚ የሆነ አድራሻ የላቸውም።

ምንም እንኳን ድምፃቸውን መስጠት የሚችሉ ታራሚዎች ቢኖሩም በባለስልጣናትና በማረሚያ ቤቶች አስተዳዳሪዎች "እብሪተኝነት" ከመምረጥ ይሰናከላሉ።

ከዚህም በተጨማሪ የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ታራሚዎች መምረጥ እንደሚችሉም ከግምት ውስጥ አያስገቡትም ወይም መብታቸውን ለማክበርና ለመተባበር ፈቃደኛ አይደሉም።

በሌላ መልኩ ስናየው በርካታ አሜሪካውያን ለመምረጥ ፍላጎቱ የላቸውም። በ2016 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከተመዘገቡት 61.4 በመቶ ናቸው የመረጡት።

ለተሻለ ፍትሃዊ ስርአት የሚሰራው ሴንቴንሲንግ ፕሮጀክት ድርጅት ከፍተኛ አማካሪ ማርክ ማውየር እንደሚሉት ከበርካታ አስርት አመታትም ጥናት በኋላም ቢሆንም በእስር ቤት ያሉ ታራሚዎች ምርጫው ቢኖራቸው ምን ያህሉ ድምፃቸውን መስጠት ይፈልጋሉ ለሚለው ግልፅ ያለ መረጃ የለም።

እሳቸው ቁጥሩ ዝቅ ያለና 10 በመቶ ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ።

ጄን ዲን በበኩላቸው ከእስር ቤቶች የሚመጣው የመራጮች ቁጥር ዝቅተኛ መሆን ታራሚዎች ግድ አይሰጣቸውም ወይም ፍላጎት የላቸውም የሚለውን አያሳይም ይላሉ።

በሚሰሩበት ኩክ ማረሚያ ቤት የመራጮች ማሽን ከመገጠማቸው በፊትም በርካታ የሴት ታራሚዎች መምረጥ እንደሚፈልጉ መረዳታቸውን ይናገራሉ።

"በሴቶች ማረሚያ ቤት ውስጥ ካሉት 74 በመቶዎቹ መምረጥ እንደሚፈልጉ ነግረውኛል" ይላሉ።

ጊዜውም ሲደርስ አንዳንዶች በጊዜ በመለቀቃቸው፣ አዳዲስ ታራሚዎች በመምጣታቸው፣ የመራጮች የምዝገባ ፎርሞች መጥፋት ወይንም በትክክል አለመሞላት ጋር ተያይዞም የተጠበቀውን ያህል ሳይሆን 20-40 የሚሆኑ ብቻ ናቸው መሞላት የቻሉት።

ይህንንም በማየት በርካቶች መምረጥ ቢፈልጉም በሚፈጠሩት ተደራራቢ እክሎች ምክንያት ለታራሚዎች መምረጥ ፈታኝ እንዳደረገው ነው።

ሂደቱንም ማቅለል እንደሚቻልም ኩክ እስር ቤት ማሽኖችን በመግጠም ምሳሌ መሆኑን ይናገራሉ።

በተለይም በርካታ እስረኞች ጥቁርና ላቲን አሜሪካውያን ወይም ደግሞ ከነጩ ውጭ ያለው ማህበረሰብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም ከፍተኛ ተፅእኖ እያደረሰ ነው።

በአሜሪካ ያሉ ጥቁር አሜሪካውያንም ሆነ ላቲን አሜሪካውያን የህዝብ ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም ግማሽ የሚሆነውን የማረሚያ ቤት ቁጥር ይዘዋል።

የአገሪቱ የፍትህ ስርአት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ፖሊስ በማሰማራት፣ በቀላልና ምክንያታዊ ባልሆኑ ጉዳዮች ለእስር በመዳረግና በሌሎች ምክንያቶች ጥቁር አሜሪካውያንና ላቲን አሜሪካውያን እንዳይመርጡ ሆነዋልም ተብሏል።

ሆኖም በርካታ ተሟጋቾች እንደሚሉት በማህበረሰቡ ዘንድ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያላቸው ዳኞች፣ የፖሊስ ኃላፊዎችና አቃቤያነ ህጎች በተመራጭነት ከመቅረባቸውም አንፃር በቀጥታ መታገል የሚቻለው በማንኛውም መንገድ ድምፅ ሲሰጥ ብቻ ነው።

ድምፅ በመስጠት ብቻ ነው ኢ-ፍትሃዊነትንም ሆነ ለቦታው ትክክለኛ ያልሆኑ ሰዎችን መታገል የሚቻለው ይላሉ።

ሬናልዶም በራሱ ተነሳሽነት መራጮችን እየቀሰቀሰ ይገኛል።

"ባገኘሁትም አጋጣሚ የመራጭነት እድል አግኝታችሁ እንዴት አትመርጡም እላለሁ?" በማለት ይጠይቃል።

ሬናልዶም በመራጭነት ሲሳተፍ ለሁለተኛ ጊዜው ነው። በመጀመሪያው ምርጫ ወቅት ገና የፍርድ ሂደቱን እየጠበቀ የነበረበት 1980ዎቹ ሲሆን በወቅቱም ቺካጎ የመጀመሪያውን ጥቁር ከንቲባ ሃሮልድ ዋሽንግተን የመረጠችበት ወቅት ነው።

"በእስር ላይ ናችሁ፤ እስር ቤት መራር እንደሆነ እናውቃለን። አስተዳደሩ ወደዳችሁም አልወደዳችሁም በህገ መንግሥቱ የተሰጣችሁ መብት ስለሆነ እንመርጣለን በሉ። ይህ ማህበራዊ ግዴታችሁ ነው" በማለት ለታራሚዎች መልእክቱን አስተላልፏል።