በአፍጋኒስታን የትምህርት ማዕከል ላይ በተፈጸመ ጥቃት 18 ሰዎች ተገደሉ

በአፍጋኒስታን መዲና ካቡል በአንድ የትምህርት ማዕከል ውስጥ በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት ቢያንስ 18 ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ በርካታ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ባለስልጣናት ገልጸዋል።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት እንዳስታወቀው ጥቃቱ የተፈጸመው በአንድ በአጥፍቶ ጠፊ ሲሆን አደጋው ደረሰው ደግሞ በግል የትምህርት ተቋም ላይ ነው።

ትምህርት ቤቱ በዋነኛነት የሸዒአ ሙስሊም ተማሪዎችን የሚማሩበት ሲሆን ብዙ ጊዜ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን በማስተናገድ የሚታወቅ ነበር።

ከቦምብ ጥቃቱ በኋላ በርካቶች ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል። ከፍንዳታው ከፍተኛነት የተነሳም የሟቾች ቁጥር እየጨመረ ሊመጣ እንደሚችል ተጠቁሟል።

ኢስላሚክ ስቴት ቡድን (አይሲስ) በማህበራዊ መገናኛ ብዙሀን በኩል ባስተላለፋቸው ምልዕክቶች ለጥቃቱ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ የገለጸ ሲሆን ጥቃቱን ስለመፈጸሙ የሚያረጋግጥ ያቀረበው ምንም ማስረጃ የለም።

ከጥቃቱ በኋላ ታሊባን እጁ እንደሌለበት አስታውቋል።

''አንድ ፈንጂ የታጠቀ አጥፍቶ ጠፊ የትምህርት ማዕከሉ ውስጥ ገባ። የጥበቃ አባላት እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት ፈንጂውን አፈነዳው'' ብለዋል የአገር ውሰጥ ጉዳዮች ሚንስቴር ቃል አቀባይ ታሪቅ አሪያን።

አሊ ራዛ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት በፍንዳታው ሕይወታቸው ያለፈው እና ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች ወደ ማዕከሉ ለመግባት በመጠባበቅ ላይ የነበሩ ናቸው።

''ከማዕከሉ በ100 ሜትር ርቀት ላይ ነበር እኔ የቆምኩት፤ ልክ ፍንዳታው ሲደርስ እኔንም ወረወረኝ'' ብለዋል።

አፍጋኒስታን ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ያስተናገደች ሲሆን አብዛኛዎቹ ጥቃቶች የተፈጸሙት ደግሞ በታሊባን ነው።

የአፍጋኒስታን ሺአ ሙስሊም ማህበረሰቦች ከዚህ በፊት በሱኒ አክራሪ ሙስሊሞች ጥቃት ይደርስባቸው ነበር። ጥቃት አድራሹ ደግሞ በብዛት አይኤስ ሲሆን የሺአ ሙስሊሞች አስተምህሮ ትክክል አይደለም ብሎ ያምናል።

እንዲህ አይነት ጥቃት በትምህርት ማዕከል ውስጥ ሲፈጸም በአፍጋኒስታን ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከዚህ በፊትም በአውሮፓውያኑ 2018 አንድ ተማሪዎች የሚያጠኑበት ማዕከል ላይ በተፈጸመ ጥቃት 48 ሰዎች መሞታቸው የሚታወስ ነው።

ከሟቾቹ መካከል አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ነበሩ። በወቅቱም አይኤስ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን ወስዶ ነበር።