የስፔን መንግሥት ጽንስ ማቋረጥን የሚመለከተውን ሕግ ሊያሻሽል ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
የስፔን መንግሥት የ16 እና የ17 ዓመት ታዳጊዎች ያረገዙትን ጽንስ ያለቤተሰቦቻቸው ፈቃድ ማቋረጥ እንዲችሉ ሕጉን መለወጥ እንደሚፈልግ ገለፀ።
የእኩልነት ሚኒስትር የሆኑት ቸይሪን ሞንቴሮ እንዳሉት ከሆነ ሴቶች "በአካላቸው ላይ የመወሰን" መብት ሊኖራቸው ይገባል።
እኤአ በ2015 ገዢው ፓርቲ ሕግ አሻሽሎ እድሜያቸው ከ16 እስከ 18 ዓመት የሆኑ ታዳጊዎች ጽንስ ለማቋረጥ የቤተሰባቸው ፈቃድ እንደሚያስፈልጋቸው ደንግጎ ነበር።
በስፔን አንዲት ሴት እርግዝናዋ እስከ 14 ሳምንት ድረስ ከሆነ ጽንሱን በሕጋዊ መልኩ ማቋረጥ ትችላለች።
ረቡዕ ዕለት ሞንቴርኖ ይህ ማሻሻያ "ከሚገባው በላይ አስፈላጊ" ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም ሌሎች ነገሮች ላይ አጽንኦት እንደሚሰጠው ሁሉ የሥነ ተዋልዶ ትምህርት እንደሚሰጥ በመናገር የጾታ ጥቃትን ለመከላከል እንደ "ክትባት" ነው ብለዋል።
ሚኒስትሯ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኮሚሽን እንዳስታወቁት የሕግ ለውጡ የእርግዝና መቆጣጠሪያ መብትን "በአዲስ ቅርጽ" ይይዛል።
መንግሥት በ2015 ገዢ የነበረው ፓርቲ ያፀደቀውን ሕግ አስወግዶ በአዲስ ለመተካት አቅዷል።
ነገር ግን ይህንን ለማድረግ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ የአብላጫውን አባላት ድጋፍ፣ 176 ድምጽ፣ ማግኘት የሚጠበቅበት ይሆናል።












