ፋሽን፡ እስራኤል የእንስሳት ፀጉር ንግድን ልታግድ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስራኤል ከዚህ በፊት ካፀደቀቻቸው ሕጎች በተጨማሪ የእንስሳት ፀጉር መግዛትም ሆነ መሸጥ ልታግድ መሆኑን አስታወቀች። ይህን በማድረግም በዓለማችን የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች።
የአገሪቷ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ጊላ ጋምሌል የእንስሳትን ቆዳ እና ፀጉር ለፋሽን ዘርፉ መጠቀም ስህተት ነበር ብለዋል።
“የፀጉር ኢንዱስትሪው በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እንስሳት እንዲገደሉ ምክንያት ሆኗል። እንዲሁም በርካታ እንስሳትም ለጭካኔና ለችግር ተዳርገዋል” ብለዋል ሚኒስትሯ።
በመሆኑም በቀጣይ የግዥ እና ሽያጭ ፈቃድ የሚሰጠውም በተቀመጠ ውስን መስፈርት መሰረት መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
የእንስሳት መብት ተሟጋቹ ቡድን ‘ፔታ’ እርምጃውን አድንቋል።
የቡድኑ ዳሬክተር ኢሊሳ አለን፤ እስራኤል የሁሉንም ጨዋ ዜጎች እሴት የሚጥሱና ከዱር እንስሳት ፀጉር የሚሰሩ ኮቶች፣ ጌጣጌጦችንና የፋሽን አልባሳት ንግድን ከግምት በማስገባት እርምጃ መውሰዷ ተገቢ ነው ብለዋል።
በእስራኤል አሁን ላይ የእንስሳት ፀጉርን መግዛትም ሆነ መሸጥ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ፈቃድ መጠየቅ ይኖርበታል።
ይሁን እንጅ አዲስ በሚወጣው ሕግ ሥር ይህ ፈቃድ የሚሰጠው ለሳይንሳዊ ምርምር፣ ለትምህርት ወይም ለመማሪያ እንዲሁም ለሃይማኖት እና ለባህል አገልግሎት ብቻ እንደሆነ ተነግሯል።
በአገሪቷ በርካታ ቁጥር ያላቸው የአይሁድ እምነት ተከታዮች በሕጉ ላይካተቱ ይችላሉ ተብሏል።
አይሁዳውያን ወንዶች ከምስራቅ አውሮፓ ባህል እንደመጣ የሚታመነውን ‘ሽትሬመልስ’ የተባለ ከፀጉር የተሰራ ክብ ኮፍያ ያደርጋሉ።
ሕጉን ተላልፎ የሚገኝ 22 ሺህ ዶላር የገንዘብ ቅጣት ወይም የአንድ ዓመት እስር ይጠብቀዋል ተብሏል።
እስካሁን ድረስ የእንስሳትን ፀጉር ሽያጭ ያገዱት ጥቂት የአሜሪካ ከተሞችና የብራዚሏ ሳኦፖሎ ናቸው።














