ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የእንግሊዙ ቤተ መፃህፍት በውሰት የተወሰዱ መፅሃፎቹ ከ48 ዓመታት በኋላ ተመለሱለት
ከቤተ መፃህፍት መፅሃፍ ተውሰው ምን ያህል ጊዜ ያቆያሉ? ሳምንታት፣ ወራት? ሳይመልሱስ ቀርተው ያውቃሉ።
በእንግሊዟ ሃምፕሻየር የሚገኝ አንድ ቤተ መፃህፍት ሁለት የህፃናት መፃህፍት ከአርባ ስምንት ዓመታት በኋላ ተመልሰውለታል።
መፅሃፎቹም ላይ መፅሃፉን በልጅነቱ የተዋሰው አንዲ የተባለው ግለሰብ "ህፃናት ሆነን ወደ ሌላ ከተማ ሄድን እናም በ1972 የተዋስነውን መፅሃፍ ሳንመልስ ቀረን፤ ለዚህም ይቅርታ እንጠይቃለን" ከሚል የይቅርታ ደብዳቤ ጋር ነው የመለሰው።
የሃምሻየር ግዛት ምክር ቤት በበኩሉ መፅሃፉ የተመለሱበት መንገድ ልብ የሚነካ ነው ያለ ሲሆን መፅሃፎቹን ለመመለስ ይህንን ያህል የዘገየበትንም ጊዜ ቅጣት እንደማይቀጡ አስታውቋል።
ምክር ቤቱ አክሎም መፅሃፎቹ በመመለሳቸው መደሰታቸውንና "የአንዲ አድራሻ ስለሌለን በቀጥታ መመለስ አልቻልንም፤ አንዲ ማወቅ ያለብህ ግን መፅሃፎቹን የመለስክበት መንገድ የቤተ መፃህፍቱን ሰራተኞች ያስደሰተና ልብ የሚነካ ድርጊት ነው" ብሏል።
መፅሃፎቹ በውሰት የዘገዩበት ጊዜ ቅጣት ይቀጡ ቢባል 8 ሺህ ፓውንድ ያህል ያስቀጣም ነበር ተብሏል።
መፅሃፎቹ ለህፃናት ቀለም አቀባብን የሚያስተምርና የባቡር መንገዶችን ታሪክ የያዘ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን ለቤተ መፃህፍቱም ባለፈው ወር በፖስታ ነው የደረሱት።