ቲክቶክ ላይ የተጣለውን እገዳ ፍርድ ቤት በጊዜያዊነት ሻረ

ቲክቶክ ከትናንት ምሽት ጀምሮ በአሜሪካ ሰዎች አውርደው እንይጠቀሙበት ገደብ ተጥሎበት ነበር።

ይሁን እንጂ የዋሽንግትን ዲሲ ዲስትሪክት ፍርድ ቤት ዳኛ ካርል ኒኮላስ እግዱን ላልተወሰነ ጊዜ ሽረውታል።

ዳኛው ይህን ውሳኔ ባያስተላልፉ ኖሮ በአሜሪካ የሚገኙ አዲስ ተጠቃሚዎች ቲክቶክን ከአፕል እና ጉገል ፕለይ ስቶር ላይ አውርደው መጠቀም አይችሉም ነበር።

መተግበሪያው በስልኮቻቸው ላይ ጭነው የሚገኙ ተጠቃሚዎችም መተግበሪያውን ማሻሻል አይችሉም ነበር ተብሏል።

ዳኛ ካርል ኒኮላስ ትናንት ምሽት የአሜሪካ መንግሥት ያስተላለፈውን ውሳኔ የሻሩት ለ90 ደቂቃ የዘለቀ አቤቱታ ካደመጡ በኋላ ነው።

ዳኛውን ይህን ውሳኔ እንዲወስኑ ያበቃቸው ምክንያት ግን ይፋ አልተደረገም።

ቲክቶክ የፍርድ ቤት ውሳኔውን አድንቆ ምብቱን ለማስጠበቅ ጥረቱን እንደሚቀጥል አስታውቋል።

"ፍርድ ቤቱ ካቀረብናቸው ሕጋዊ መከራከሪያዎች ጋር መስማማቱ አስደስቶናል" ብሏል ቲክቶክ ባወጣው የጽሑፍ መግለጫ።

ቲክቶክ ከአፕል እና ጉግል ፕለይ ስቶር ላይ መተግበሪያውን ማንሳት ከአሜሪካ ሕገ-መንግሥት ጋር የሚቃረን ነው ብሎ አጥብቆ ሲከራከር ቆይቷል።

ሰዎችም ቲክቶክን እንዳይቀላቀሉ መከልከሉ የሰዎች የመናገር መብት የሚጥስ ነው ይላል።

የአሜሪካ መንግሥት ጠበቆች በበኩላቸው ቲክቶክ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ጉዳይ አስፈጻሚ ነው ሲሉ ይከሱታል።

ብሔራዊ ደህነት

በአሁኑ ወቅት ቲክቶክ በአሜሪካ የሚኖረው የወደፊት እጣ ፈንታ ግልጽ አይደለም። በቻይናው ኩባንያ ባይቴንዳንስ ባለቤትንት የሚተዳደረው ቲክቶክ ለአሜሪካ ብሔራዊ ስጋት ነው የሚል ክስ ይቀርብበታል።

የፕሬዝደንት ትራምፕ አስተዳደር ባይቴንዳንስ የአሜሪካውያንን ግላዊ መረጃ እየሰበሰበ ለቻይናው ኮሚኒስት ፓርቲ ያቀርባል ይላል።

ባይቴንዳንስ በበኩሉ የመተግበሪያው ተጠቃሚ ሰዎች መረጃ በአሜሪካ እና በሲንጋፖር የሚከማች መሆኑን እና ለቻይና ሕጎች ተገዢ አልመሆኑን ይጠቅሳል።

ቲክቶክ በአሜሪካ የሚኖረው እጣ ፈንታ ጥያቄ ውስጥ ወድቆ በሚገኘበት ወቅት፤ ቲክቶች ኦራክል እና ዎልማርት ለተሰኙት ሁለት ግዙፍ የአሜሪካ ጉባንያዎች የ20 በመቶ ድርሻውን ሊሸጥ መሆኑን አስታውቋል።

ትራምፕ ግን ባይቴንዳንስ የበለይነትን የሚወስድበት ስምምነት በአስተዳደራቸው ውስጥ ተቀባይነት እንደሌላው ተናግረዋል።