ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ በአሜሪካ ጽንስ ማቋረጥ ወንጀል ሊሆን እንደሚችል ጠቆሙ
ፕሬዝደንት ትራምፕ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እአአ 1973 ላይ ጽንስ ማቋረጥን ሕጋዊ ያደረገውን ውሳኔ ተመልሶ ሊያጤነው እንደሚችል ጠቆሙ።
ትራምፕ በእሳቸው እጩነት የቀረቡት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ የጽንስ ማቋረጥ ሕጋዊነትን ፍርድ ቤቱ ደግሞ እንዲያይ በማድረጉ ላይ ተሳትፎ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ኤሚ ባሬት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ አድርገው ሲመርጡ ስለ ጽንስ ማቋረጥ ሕግ ዙሪያ ቀድመው እንዳልተወያዩ ተናግረዋል።
ኤሚ ባሬት "በአመለካከቷ ወግ አጥባቂ ነች" ብለዋል ትራምፕ።
በትራምፕ እጩ ሆነው የቀረቡት ወግ አጥባቂዋ ኤሚ ባሬት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እአአ 1973 ላይ ጽንስ ማቋረጥ ሕጋዊ ነው ብሎ የወሰነውን ውሳኔ እንዳያሽሩት ስጋት እንዳላቸው የሴቶች መብት ተከራካሪ ዴሞክራቶች ይናገራሉ።
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት 9 የሕይወት ዘመን ዳኞች ያሉት ሲሆን የኤሚ ባሬት ሹመት የሚረጋገጥ ከሆነ ከአጠቃላይ 9 የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች መካከል የወግ አጥባቂ ዳኞች ብዛት ወደ 6 ከፍ ይላል።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኛ ሆነው የሚሾሙ ዳኞች ሙሉ የዕድሜ ዘመናቸውን ማገልገል ይችላሉ። በጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚያስተላለፉት ውሳኔም በአገሪቱ ፖሊስ እና ስትራቴጂዎች ላይ ተጽእኖ የሚያሳድር ነው።
ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቅርቡ ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች መካከል በሁሉም 50 የአሜሪካ ግዛቶች የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን መፍቀድ እና ትራምፕ አስተላልፈው የነበረውን የጉዞ ገደብ ማስቆም ተጠቃሽ ናቸው።
እአአ 1973 ላይ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጽንስ ማቋረጥ ሕጋዊ ነው ሲል 7 ለ2 በሆነ ድምጽ ወሰኗል።
ፍርድ ቤቱ ከዚህ ውሳኔ የደረሰው ሴቶች እርግዝናን የማቋረጥ መብታቸው ከግል የፍላጎት ነጻነት የሚመነጭ መሆኑ እና ይህም በአሜሪካ ሕገ-መንግሥት ውስጥ የተንጸባረቀ ነው በማለት ነው።
ኤሚ ኮሬት ባሬት ማን ናቸው?
የ48 ዓመቷ ዳኛ ጠንካራ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ናቸው። ጽንስ ማቋረጥን አጥብቀው ይቃወማሉ።
ከዚህ ቀደም በጻፉት ጽሑፍ ላይ የሰው ልጅ ሕይወት የሚጀምረው ከተጸነሰበት ቅጽበት ጀምሮ ነው ብለዋል። ስለዚህ ጽንስ ማቋረጥ ከንፍስ ማጥፋት አይተናነስም ብለው ያምናሉ፡፡
ይህ የዳኛዋ አቋም በአሜሪካ ጽንስ ማቋረጥ ሕጋዊ መሆኑ እንዲቀር በሚሹ ሰዎች ዘንድ ደስታን ፈጥሯል።
ኢንዲያና ግዛት ውስጥ ከሚገኘው ኖተር ዳም ዩኒቨርሲቲ በሕግ የተመረቁት ዳኛ የትራምፕ ጠንካራ የጸረ- ስደተኞች ፖሊስ ደጋፊ መሆናቸው ይነገራል።
አሜሪካውያን የጦር መሳሪያ የመታጠቅ መብት አላቸው የሚል ጽኑ አቋም እንዳላቸውም ይገለጻል።
የ7 ልጆች እናት የሆኑት ኤሚ ቤሬት በተማሩበት ዩኒቨርሲቲም ለ15 ዓመታት አስተምረዋል።