ማሊ፡ በቅርቡ መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደባት ማሊ የሲቪል መሪዋን በዓለ ሲመት አካሄደች

ከአምስት ሳምንታት በፊት ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ባውባካር ኬታን በመፈንቅለ መንግሥት ያስወገደችው ማሊ በዛሬው እለት የሲቪል መሪዋን በዓለ ሲመት አካሂዳለች።

የሲቪል መሪው ባህ ንዳው የ70 አመት ዕድሜ ባለፀጋ ሲሆኑ ከዚህ ቀደም የመከላከያ ሚኒስትር ነበሩ። እሳቸው የማሊ መሪ እንዲሆኑ የተመረጡትም በመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ በሆኑት ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ ነው።

ባህ ንዳው በቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት በሄሊኮፕተር ፓይለትነት የሰለጠኑ ሲሆን በተለያዩ የስልጣን እርከኖችም አገራቸውን አገልግለዋል።

በመፈንቅለ መንግሥት የተነሱት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ስርም የመከላከያ ሚኒስትር ነበሩ። ከፕሬዚዳንቱም ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ከአምስት አመት በፊት ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል።

የሲቪል መሪውም የሽግግር መንግሥቱን ቀጣዩ ምርጫ እስኪያደርግ ድረስም ይመራሉ። ምርጫውም በአስራ ስምንት ወራት ውስጥ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

ኮሎኔል ጎይታም ምክትል ፕሬዚዳንት ይሆናል ተብሏል።

ማሊ አባል የሆነችበትና አስራ አምስት አባላት ያሉት የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ማሊ የሲቪል መሪዋን ካልመረጠች የተጣለው ማዕቀብ አይነሳም ብሎ ነበር።

በመዲናዋ ባማኮ የጥሬ እቃዎች እጥረት አጋጥሟል የተባለ ሲሆን የኢኮዋስ ማዕቀብ በቅርቡ የሚነሳም ከሆነ የንግድ እንቅስቃሴ ወደቀደመው ጊዜ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የተደረገው የማሊ መፈንቅለ መንግሥት በርካታ ማሊያውያንን ያስደሰተ ቢሆንም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ የበርካታ አገራት መሪዎች ሲያወግዙት የአፍሪካ ህብረት ደግሞ ከአባልነት አግዷታል።

ሰፊ የቆዳ ሽፋን ያላት ማሊ ግዛቷ የሰሃራ በረሃንም የተወሰነ የሚሸፍን ሲሆን የፈረንሳይ ወታደሮችን ጨምሮ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪዎች አክራሪ ፅንፈኝነትን እንዋጋለን በሚልም ሰራዊት አስፍረውባታል።

ለባለፉት ሁለት ወራት ያህል የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከፍተኛ ህዝብ የተሳተፈባቸውን የተቃውሞ ሰልፎች መርተዋል።

በሃገሪቱ ውስጥ ያለውን ሙስና፣ የምጣኔ ኃብት ኢ-ፍትሃዊ ክፍፍልና አወዛጋቢ የምርጫ ህግን በተመለከተ ተቃውሞን ከማሰማት ባለፈ የሁሉም መሰረታዊ ጥያቄ ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን እንዲወርዱ ነበር።

እነዚህን የተቃውሞ ሰልፎች በዋነኝነት ሲያስተባብሩ የነበሩት ኢማም ማህሙድ ዲኮም ነበሩ። ኢኮዋስ በአሸማጋይነትም በመግባት ህዝቡ የሚጠይቃቸውን ማሻሻያዎች ፕሬዚዳንቱ ተግባራዊ እንዲያደርጉም ሞክሯል።

በዚህም ሁኔታ እያለ ነው የወታደራዊውን ኃይል የሚመሩ ኮሎኔሎችና ጄኔራሎች ተሰባስበው የፕሬዚዳንቱን ስልጣን ለማሳጠር የወሰኑት።

ሆኖም ኢ-ህገ መንግሥታዊ በሆነ ሁኔታ የስልጣን መገርሰስን ኢኮዋስ አልተቀበለውም።

ሆኖም ማሊያውያን በተለይም በደቡብና ማዕከላዊ ማሊ የሚኖሩ ማሊያውያን የፕሬዚዳንቱ ከስልጣን መውረድ አስፈንድቋል።

አስተዳደራቸው በርካታ የሙስና ቅሌቶችን ማስተናገድ ብቻ ሳይሆን የመስረተ ልማቶች ችግር ብዙዎችን አስመርሯል። በተለይም አርሶ አደሮች የማዳበሪያ እጥረት ማጋጠሙ ቀውስን አስከትሏል።

ከዚህም በተጨማሪ የሃገሪቱ ሰራዊት ፅንፈኛ አክራሪዎች ጋር በሚያደርገው እልህ አስጨራሽ ትግል የሚከፈላቸው ክፍያ ትንሽ መሆኑ ቁጣን ፈጥሯል።