ልደቱ አያሌው ፡ "እኛ አቶ ልደቱን አላሰርንም በአደራ ነው እዚህ የተቀመጡት አሉን" የኢዴፓ ፕሬዝደንት አቶ አዳነ ታደሰ

አቶ ልደቱ አያሌው

በትናንትናው ዕለት [ማክሰኞ] የምሥራቅ ሸዋ ዞን ፍርድ ቤት አቶ ልደቱ አያሌው በአንድ መቶ ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲወጡ ቢወስንም እንዳልተፈቱና ፖሊስ ሊፈታቸው ፈቃደኛ አለመሆኑን የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት አቶ አዳነ ታደሰ ለቢቢሲ አመሻሹን ተናግረዋል።

"ፖሊስ ሊፈታ ፈቃደኛ አይደለም። እስከነጭራሹ ሊያናግሩን ፈቃደኛ አይደሉም። ቢሯቸውን ጥለው ጠፉ። ማንም የሚያናግረን አጣን" ያሉት አቶ አዳነ

ከቢሾፍቱ ተመልሰውም ወደ አዲስ አበባ እየመጡ እንደሆነ አስረድተዋል።

የምሥራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለሁለት ወር ያህል በእስር ላይ ያሉት አቶ ልደቱ በዋስ እንዲለቀቁ ለቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የፃፈ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰዋል።

ደብዳቤውንም በአባሪነት በመያዝ የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ ኃላፊዎችን ቢያናግሩም "እኛ አቶ ልደቱን አላሰርንም በአደራ ነው እዚህ የተቀመጡት ስለዚህ ይህንን የሚመራ ግብረ ኃይል አዳማ ላይ አለ፤ እዚያ ሄዳችሁ ጠይቁ" የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።

አቶ ልደቱ የት እንዳሉም በሚጠይቁበት ወቅትም ዐቃቤ ሕግ የሚመለከት ጉዳይ ነው የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸውም አቶ አዳነ ይናገራሉ።

ይህንንም ተከትሎ ወደ ምሥራቅ ሸዋ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ በማቅናት ሲጠይቁም "እንደዚህ ብሎ ነገር የለም እንዲፈቱ የታዘዘው የከተማው ፖሊስ መምሪያ ነው፤ ስለዚህ የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መከበር አለበት። እኛ በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም የምንለው ነገር የለም ሄዳችሁ ንገሩ አሉን" ብለው እንደመለሷቸውም አቶ አዳነ ያስረዳሉ።

ወደ ቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ተመልሰው የመምሪያውን አዛዥ ኮማንደር ደረጀን ቢጠይቁም በተመሳሳይ መልኩ እነሱ አቶ ልደቱን እንዳላሰሩ እንደነገሯቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

"አቶ ልደቱን እኛ አላሰርንም፤ እዚህ የተቀመጡት በአደራ ነው። ስለዚህ ከሚመለከታቸው አካል ጋር ተነጋግረን መልስ እንሰጣችኋለን" ያሏቸው ሲሆን ከሰዓት በኋላ ወደ 7፡30 እንዲመለሱም ቀጠሮ ሰጥተዋቸው እንደነበር ተናግረዋል።

በቀጠሯቸው መሰረትም ከ7፡30 እስከ 11 ሰዓት ድረስ ቢቆዩም አዛዡንም ሆነ ሌሎች አመራሮችን ማግኘት አለመቻላቸውንና ጥሩ ምላሽ እንዳልሰጣቸው ይናገራሉ።

"የአቶ ልደቱ መርማሪ የነበረውን ኮማንደር አግኝተን ልናናግረው ሞክርን። እኔ አይመለከተኝም ብሎ አመናጭቆን ሄደ" ብለዋል አቶ አዳነ ።

ፕሬዚዳንቱ በነገ [ሐሙስ] አዳማ ከተማ ላይ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ተፈፃሚ አለመሆኑንም አስመልክቶ አቤቱታቸውንም ለማቅረብ ማቀዳቸውን ገልፀዋል።

የሙዚቀኛ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በቢሾፍቱ ከተማ የተፈጠረውን ሁከት በማነሳሳት፣ መምራትና በገንዘብ መደገፍ ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ልደቱ አያሌው ጉዳያቸውን ሲያይ የነበረው ፍርድ ቤት ክሳቸውን ቢዘጋም እንገደና ያልተፈቀደ የጦር መሳሪያ በመያዝ ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ክሱ ከዚህ በፊት ሲታይ ከነበረበት የቢሾፍቱ ከተማ በመውጣት በአዳማ ከተማ በሚገኝ ፍርድ ቤት እየታየ የነበረ መሆኑ ይታወሳል።