ስፖርት፡ ሶማሊያን በኦሎምፒክስ መወከል ህልሟ የሆነው የእንግሊዝ የቦክስ ሻምፒዮናዋ ራምላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩናይትድ ኪንግደም የቦክስ ሻምፒዮና ለመሆን የበቃችው ትውልደ ሶማሊያዊቷ ራምላ አሊ ከሰሞኑ የፕሮፌሽናል ቦክስ ህይወቷን ለመጀመር ማች ሩም ከተባለው የአለም ምርጡ ስፖርት አስተዋዋቂ ኩባንያ ጋር ተፈራርማለች።
የ31 አመቷ ራምላ በሶማሊያ የነበረውን የእርስ በርስ ጦርነት ሸሽታ ነው በስደት እንግሊዝ የገባችው። ስለ ቦክስ ህይወቷም ቤተሰቦቿ የሚያውቁት አልነበረም።
በቦክስ ስፖርት በኦሎምፒክ በመሳተፍ የመጀመሪያዋ ሶማሊያዊት ለመሆን ያለመችው ራምላ የፕሮፌሽናል የቦክስ ህይወቷንም በጥቅምት ወር ትጀምራለች።
ራምላ የቦክሰኝነት ጉዞዋ ሃ ብሎ የተጀመረው በአስራዎቹ እድሜ እያለች ሲሆን በወቅቱም ከቤተሰቦቿ ጋር በስደት እንግሊዝ የገቡበት ወቅት ነበር።
"የአለም ሻምፒዮና መሆን እፈልጋለሁ፤ በዚህም አለም ሶማሊያን በተለየ መንገድ እንደሚያዩዋት ተስፋ አደርጋለሁ"ትላለች።
በሶማሊያ የርስ በርስ ጦርነት የ12 አመት ወንድሟ ከተገደለ በኋላ ቤተሰቦቿ ከመዲናዋ ሞቃዲሾ ወደ ኬንያ፣ ናይሮቢ ተሰደዱ።
በናይሮቢ ቆይታቸውም ወቅት ሰውነቷ ወፍራም ስለነበር የሚያፌዙባትና የሚያሾፉባት ነበሩ።
ቤተሰቡ ወደ ለንደንም በስደተኝነት ከመጡ በኋላ በአካባቢዋ ወደሚገኝ ጂምናዚየም ሄዳ በቦክስ መሰልጠን ጀመረች።
ለቤተሰቧቿም ለመንገር አልደፈረችም ምክንያቱም ስፖርት ለሙስሊም ሴት አይሆንም ብለው ይከለክሉኛል በሚልም ነበር።
በድብቅም መሰልጠኗን ቀጠለች በ2016 ዩናይትድ ኪንግደምን በመወከል ስታሸንፍም ለቤተሰቦቿ ለሩጫ ልወጣ ነው ብላ ነው የነገረቻቸው።
በ2017ም የትውልድ ሃገሯን ሶማሊያን ነው የምወክለው በማለትም ቀየረች።
በአሁኑ ሰዓት እናቷም ቢሆኑ ለቦክስ ሙያዋ ከፍተኛ ድጋፍ ያላቸው ሲሆን የሚያሰለጥናትም ባለቤቷ ሪቻርድ ሙር ነው።
በመጪዎቹም የፕሮፌሽናል ቦክስ ውድድሮችን ታካሂዳለች።
ሆኖም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተራዘመው ኦሎምፒክስ ዋነኛ ህልሟ ነው። የቦክስ ኦሎምፒክስ በያዝነው አመት ሃምሌ ወር ይካሄዳልም ተብሎ ይጠበቃል።
"የፕሮፌሽናል የቦክስ ህይወቴን የመጀመሪያ ወቅቱ አሁን ነው። በኦሎምፒክስ ለመሳተፍ ስጠብቅ ላልወዳደርም እችላለሁ። ኦሎምፒክስ ደግሞ በአሁኑ ሁኔታ መካሄዱን እርግጠኛ አይደለም" የምትለው ራምላ
"የኦሎምፒክ ህልሜ አሁንም እንዳለ ነው ሆኖም የፕሮፌሽናል የስፖርት ጉዞዬን መጀመሬም አስደሳች አድርጎልኛል" ትላለች።
ቦክሰኛዋን የሚያስታዋውቃት ድርጅት ባለቤት የሆነው ኤዲ ኸርን እንደሚለው "የራምላ ታሪክ አስደናቂና በርካቶችንም የሚያነሳሳ ነው። እዚህ ለመድረስ በርካታ ውጣ ውረዶችን አይታለች"
ራምላ በአለም ላይ አሉ የሚባሉ ሴት ቦክሰኞችን በማስተዋወቅ የሚታወቀው ማችሩም ስፖርትን በመቀላቀሏ ደስተኛ እንደሆነ የሚናገረው ኤዲ ኸርን የሶማሊያ የመጀመሪያ የአለም ሻምፒዮናነትንም ህልም ለማሳካት የተመረጠ ቦታ ነው ብሏል።












