"ትራምፕ አገሪቷን እንደ ስምንት አመት ህፃን ነው እየመሯት ያሉት" ኢልሃን ኦማር

የፎቶው ባለመብት, Stephen Maturen
ትውልደ ሶማሊያዊቷ የአሜሪካ የህግ መምርያ ምክር ቤት አባል ኢልሃን ኦማር ዶናልድ ትራምፕን "አገሪቷን እንደ ስምንት አመት ህፃን እየመሯት ነው" በማለት ተችታቸዋለች።
ኢልሃን ይህንን ያለችው በትናንትናው ዕለት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅስቀሳ ዘመቻቸው ስሟን ጠርተው ለደጋፊዎቻቸው ያደረጉትን ንግግር ተከትሎ ነው።
"በሚኒሶታ የሚደረገውን ምርጫ በሷ ምክንያት እናሸንፋለን። አገራችንን እንዴት መምራት እንዳለብን ልትነግረን ትፈልጋለች። የመጣሽበት አገር ምን አደረግሽ? አገርሽ እንዴት ናት?"
በማለት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስደተኝነቷን ለማስታወስ ሞክረዋል።
ኢልሃንም በምላሹ
"በመጀመሪያ ደረጃ አሜሪካ አገሬ ናት። በስልጣን እያሉም ክስ እንዲጀመርብዎ የወሰነው የምክር ቤት አባልም ነኝ። በሁለተኛ ደረጃ እኔ ከአገሬ የተሰደድኩት በስምንት አመቴ የርስ በርስ ጦርነትን ሸሽቼ ነው። የስምንት አመት ልጅ አገርን አይመራም፤ ነገሩ ግን አገሪቷን የሚመሩት እንደ ስምንት አመት ልጅ ነው" በማለት የዲሞክራት አባሏና በትራምፕ ላይ የሰላ ትችት በመሰንዘር የምትታወቀው ኢልሃን በትዊተር ገጿ አስፍራለች።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
በሶማሊያ የተወለደችው ኢልሃን የሶማሊያ የርስ በርስ ጦርነትን ተከትሎ ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ አሜሪካ የተሰደደችው እንደ ጎሮጎሳውያኑ አቆጣጠር በ90ዎቹ ነው።
በ2016ም የሚኒሶታ ግዛትን በመወከል የመጀመሪያዋ ትውልደ ሶማሊያዊት የህግ መምሪያ ምክር ቤት አባል መሆን ችላለች።
የሚኒሶታ ግዛት ህዳር ላይ በሚደረገው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ላይ ከፍተኛ ፍልሚያ የሚደረግበትም ነው ተብሎ ይጠበቃል።












