ዩቲዩብ ቲክቶክ መሰል መተግበሪያ ሕንድ ውስጥ ሊጀምር ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዩቲዩብ የተሰኘው ግዙፍ ማሕበራዊ ድር አምባ ሕንድ ውስጥ ቲክቶክን ይቀናቀናል የተባለ መተግበሪያ ይፋ ሊያደርግ መሆኑን አስታውቋል።
ዩቲዩብ ሾርትስ የተሰኘ ስም የተሰጠው መተግበሪያ ተንቀሳቃሽ ምስሎች መጋሪያ ነው።
ተጠቃሚዎች ከ15 ሰኮንድ የረዘመ ምስል እንዲጭኑ አይፈቀድላቸውም።
መተግበሪያ ከቻይናው ቲክቶክ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ቴክኖሎጂ እንደሚጠቀምም ታውቋል።
ሕንድ ባለፈው ሰኔ ከቻይና ጋር ድንበር ላይ መጋጨቷን ተከትሎ ቲክቶክ የተሰኘው አነጋጋሪ የተንቀሳቃሽ ምስል መጋሪያ ድር አምባን ጨምሮ ሌሎች 58 መተበግሪያዎችን ማገዷ አይዘነጋም።
በወቅቱ ቲክቶክ ሕንድ ውስጥ በዓለም ትለቁ የተባለ ገበያ ነበረው። የተጠቃሚዎች ቁጥርም 120 ሚሊዮን ገደማ ነበር።
ዩቲዩብ ሕንድ ውስጥ የቲክቶክን ክፍተት ለመሙላት ጥቅም ላይ መዋል ከጀመሩ ሃገር በቀል ድርጅቶችም ፉክክር ይጠብቀዋል።
የዩቲዩብ ምርቶች ቁጥጥር ምክትል ፕሬዝደንት የሆኑት ክሪስ ጄፍ እንዳሉት ሾርትስ የተሰኘው አዲስ ቴክኖሎጂ ዋና ዓላማው ተጠቃሚዎች ሞባይል ስልካቸውን ብቻ ተጠቅመው አጠር ያሉ ማራኪ ቪድዮዎችን እንዲሠሩ ማመቻቸት ነው።
አዲሱ ቴክኖሎጂ የተለያዩ ካሜራዎችን ተጠቅሞ ቪድዮዎችን መሥራት ያስችላል።
አልፎም ተጠቃሚዎች ከሙዚቃ ቤተ መዘክር የፈለጉትን ሙዚቃ ተጠቅመው መጠቀም እንዲችሉ ያደርጋል።
ምክትል ፕሬዝደንቱ ሾርትስ በደንብ እየተሻሻለ ሲመጣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ተገጥመውለት ወደ ሌሎች ገበያዎች እንደሚሠራጭ ተናግረዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ቻይና ሠራሹ ቲክቶክ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እንዳይሠራ አደርጋለሁ ማለታቸውን ተከትሎ በርካታ አማራጮች ወደ ገበያ መምጣት ጀምረዋል።
ፕሬዝደንቱ የተጠቃሚዎች ግላዊ መረጃ በቲክቶክ አማይነት ለቻይና መንግሥት ተላልፎ እየተሰጠ ነው ይላሉ።
የሕንድ መንግሥትም ተመሳሳይ ቅሬታ በማቅረብ ነው ቲክቶክን ከጥቅም ውጭ ያደረገው።












