ደቡብ አፍሪካ፡ በጥቁሮች ከርዳዳ ጸጉር ላይ የተሳለቀው ማስታወቂያ ቁጣን ቀሰቀሰ

ማስታወቂያውን እየተቃወሙ ያሉ ደቡብ አፍሪካውያን

የፎቶው ባለመብት, AFP

በደቡብ አፍሪካ ክሊክስ የተባለ የውበት እቃዎች አምራችና አከፋፋይ ኩባንያ በሰራው የድረገጽ ማስታወቂያ ደንበኞቹን አስቆጥቷል፡፡

ሞገደኛው የተቃዋሚ መሪ ጁሊየስ ማሌማ ደቡብ አፍሪካዊያን ለተጨማሪ ተቃውሞ እንዲነሱ አሳስቧል፡፡

ክሊክስ ኩባንያ ሁሉንም የችርቻሮ መደብሮች ለ5 ቀናት እንዲዘጋ አሳስቧል፡፡

ሰኞ ዕለት የጁሊየስ ማሌማ ፓርቲ ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ የጠራውን ተቃውሞ ተከትሎ 400 ሱቆችን ለመዝጋት ተገዷል፤ ድርጅቱ፡

የድርጅቱ ብዙዎቹ የችርቻሮ መደብሮቹ በተቆጡ ዜጎች ተሰባብረውበታል፡፡

ክሊክስ ይህንን መአት ያወረደበትን ማስታወቂያ ለምን እንዳስነገረ ግልጽ አይደለም፡፡

በዚህ በድረገጹ በለቀቀው ማስታወቂያ የአፍሪካ ከርዳዳ ጸጉር አስቀያሚ እንደሆነና የፈረንጆች ጸጉር ግን በጣም ጤናማ አድርጎ ገልጾታል፡፡

ይህ ማስታወቂያ ወዲያውኑ ከኩባንያው ገጽ እንዲወርድ የተደረገ ሲሆን ኩባንያውም ጥቁሮችን ከባድ ይቅርታ ጠይቋል፡፡ በዚህ ሥራ የተሳተፉትም ዋጋቸውን ያገኟታል ብሏል፡፡

የማሌማ ፓርቲ ግን በዚህ የተሳተፉት ሰዎች ስም ዝርዝር እንዲታተም እና ከሥራም እንዲባረሩ ጠይቋል፡፡

መንግሥት የተቆጡ ዜጎችን ነገር አብርዱ፤ ንብረት አታውድሙ እያላቸው ነው፡፡

'እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ጥቁሮች ከነጮች ያነሱ መሆናቸውን የሚያመላክቱ ናቸው። የነጮች የውበት መለኪያ በጣም የሚፈለግና የሚወደድ እንዲሁም የጥቁሮች ደግሞ የማይረባ ተደርጎ ነው የቀረበው።'' በማለት የጁሊየስ ማሌማ ፓርቲ መግለጫ አውጥቷል።

የዚሁ ፓርቱ አባላት በአውሮፓውያኑ 2018 ተመሳሳይ ተቃውሞ ያካሄዱ ሲሆን በወቅቱ 'ኤችኤንድኤም' የተሰኘው ግዙፍ የልብስ አምራች ኩባንያ በለቀቀው አንድ ማስታወቂያ ላይ አንድ ጥቁር ታዳጊ 'ጫካው ውስጥ የምገኝ ምርጥ ጦጣ ነኝ' የሚል ለብሶ መታየቱን ተከትሎ ነበር።

''እንደዚህ አይነት አስጸያፊና የሰዎችን ስሜት የሚጎዳ ማስታወቂያ በድረገጻችን ላይ እንዲለቀቅ በመፍቀዳችን በጣም አዝኛለሁ'' ብሏል የክሊክስ ኃላፊ ቪኬሽ ራምሱንደር።

አክሎም ስራቸውን በአግባቡ ያልተወጡ ሰራተኞች እንዲታገዱ መደረጋቸውን አስታውቋል።

ነገር ግን የኃላፊው የይቅርታ መልዕክት ያላጠገባቸው የኢኤፍኤፍ በርካታ ደጋፊዎች በመላው አገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ ሱቆችን ከበዋል።

በትዊተር በተሰራጩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ላይ በርካታ የድርጅቱ ሱቆች ተዘግተው የሚታይ ሲሆን በአንዳንድ ሱቆች በር ላይ ደግሞ የጥበቃ ሰራተኞች ተቃዋሚዎቹ ወደ ውስጥ እንዳይገቡ ሲከለክሉ ይታያል።

በሌላ ተንቀሳቃስ ምስል ላይ ደግሞ የፓርቲው ደጋፊዎች የአንድን ሱቅ የልብስ መደርደሪያዎች ሲጎትቱ ተስተውሏል።