ደቡብ አፍሪካ፡ የዘረኝነት መልዕክት ያለው ማስታወቂያ ያሰራው ፀጉር ቤት እንዲዘጋ ተገደደ

ክሊክስ የለቀቀው ማስታወቂያ ባሳለፍነው ሳምንት በድረገጹ ላይ የነበረ ሲሆን አሁን ግን እንዲወርድ ተደርጓል

የፎቶው ባለመብት, EFF

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የዘረኝነት መልዕክት ያለው ማስታወቂያ አሰርቷል የተባለው የጤና እና የውበት ሳሎን ድርጅት የተለያዩ ቅርንጫፎች በተቃዋሚዎች እንዲዘጉ መደረጋቸው ተዘግቧል።

'ክሊክስ' የተባለው ድርጅት ባሰራው ማስታወቂያ ላይ የጥቁሮች ቆዳ እንደ ደረቅና የተጎዳ ተደርጎ የቀረበ ሲሆን የነጮች ጸጉር ግን በጣም ጥሩ እንደሆነና ሉጫ መሆኑ ታይቷል።

'ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ' ወይንም በምጽሀረ ቃል 'ኢኤፌኤፍ' በመባል የሚታወቀው የደቡብ አፍሪካ ተቃዋሚ ፓርቲ ማስታወቂያውን ዘረኛና የሰዎችን ማንንት የሚያንቋሽሽ ነው ብሎታል።

የፓርቲው መሪ ጁሊየስ ማሌማ የድርጅቱ ሱቆች እንዲዘጉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ምንም እንኳን ድርጅቱ በፓርቲው ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ቢዝትም ጁሊየስ ማሌማ ግን ደጋፊዎቻቸው 'ለፍልሚያ ዝግጁ' እንዲሆኑ በማሳሰብ ፓርቲያቸው በማስፈራራቶች አርፎ እንደማይቀመጥ ገልጸዋል።

''እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ጥቁሮች ከነጮች ያነሱ መሆናቸውን የሚያመላክቱ ናቸው። የነጮች የውበት መለኪያ በጣም የሚፈለግና የሚወደድ እንዲሁም የጥቁሮች ደግሞ የማይረባ ተደርጎ ነው የቀረበው። የጥቁሮች ጸጉር ቶሎ ይበላሻል፣ ይበሰብሳል እንዲሁም ችግር አለበት የሚል መልዕክት ነው የተላለፈው'' በማለት የጁሊየስ ማሌማ ፓርቲ መግለጫ አውጥቷል።

የዚሁ ፓርቱ አባላት በአውሮፓውያኑ 2018 ተመሳሳይ ተቃውሞ ያካሄዱ ሲሆን በወቅቱ 'ኤችኤንድኤም' የተሰኘው ግዙፍ የልብስ አምራች ኩባንያ በለቀቀው አንድ ማስታወቂያ ላይ አንድ ጥቁር ታዳጊ 'ጫካው ውስጥ የምገኝ ምርጥ ጦጣ ነኝ' የሚል ለብሶ መታየቱን ተከትሎ ነበር።

ክሊክስ የለቀቀው ማስታወቂያ ባሳለፍነው ሳምንት በድረገጹ ላይ የነበረ ሲሆን አሁን ግን እንዲወርድ ተደርጓል።

''እንደዚህ አይነት አስጸያፊና የሰዎችን ስሜት የሚጎዳ ማስታወቂያ በድረገጻችን ላይ እንዲለቀቅ በመፍቀዳችን በጣም አዝኛለሁ'' ብሏል የክሊክስ ኃላፊ ቪኬሽ ራምሱንደር።

አክሎም ስራቸውን በአግባቡ ያልተወጡ ሰራተኞች እንዲታገዱ መደረጋቸውን አስታውቋል።

ነገር ግን የኃላፊው የይቅርታ መልዕክት ያላጠገባቸው የኢኤፍኤፍ በርካታ ደጋፊዎች በመላው አገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ ሱቆችን ከበዋል።

በትዊተር በተሰራጩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ላይ በርካታ የድርጅቱ ሱቆች ተዘግተው የሚታይ ሲሆን በአንዳንድ ሱቆች በር ላይ ደግሞ የጥበቃ ሰራተኞች ተቃዋሚዎቹ ወደ ውስጥ እንዳይገቡ ሲከለክሉ ይታያል።

በሌላ ተንቀሳቃስ ምስል ላይ ደግሞ የፓርቲው ደጋፊዎች የአንድን ሱቅ የልብስ መደርደሪያዎች ሲጎትቱ ተስተውሏል።