ጤና፡ኮሮናቫይረስን ለማከም ምን ያህል ተቃርበናል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለኮቪድ-19 የሚሆን ህክምናም ሆነ ክትባት ለማግኘት በመላው ዓለም የሚገኙ ተመራማሪዎችና ድርጀቶች ደፋ ቀና ማለት ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ለመሆኑ ለዚህ ወረርሽኝ መድሀኒት ለማግኘት ምን ያህል ተቃርበን ይሆን?
ከ150 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የመድሀኒት አይነቶች በበርካታ አገራት ለማምረት ጥረት እየተደረገ ሲሆን አብዛኛዎቹ መድሃኒቶች ከዚህ በፊት የነበሩና ኮቪድ-19ኝን ለማከም ይረዳሉ አይረዱም የሚለው ምርምር የሚካሄድባቸው ናቸው።
- ዩኬ በዚህ ዘርፍ በዓለም ትልቅ የተባለውን ክሊኒካል ሙከራ እያደረገች ነው። ሙከራው 'ሪከቨሪ' የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ከ12 ሺ በላይ ታማሚዎች እየተሳተፉበት ይገኛሉ። በሙከራውም መድሀኒቶቹ ምን አይነት ተፍህኖ እንደሚኖራቸው ይታወቃል ተብሏል።
- • የዓለም ጤና ድርጅትም መድሀኒት በማግኘቱ ሂደት ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረገ ነው። በዚሁም በበርካታ አገራት ተስፋ ሰጪ የሆኑ መድሃኒቶችን እየሞከረ እንደሆነ አስታውቋል።
- ጥቂት የማይባሉ የመድሃኒት አምራች ግዙፍ ኩባንያዎችም ቢሆኑ ለኮቪድ-19 የሚሆኑ መድሂቶችን ለማግኘት እየሰሩ ነው።
ክትባት ለማግኘት ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ በኮሮረናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ለማከም የሚውሉ መድህኒቶችን የመስራት ሂደቱ ሶስት ዋነኛ መንገዶችን እንደሚከተል ባለሙያዎች ገልጸዋል።
- 'አንቲቫይራል' የሚባሉት የመድሀኒት ኤእነቶች ሲሆኑ ኮሮናቫይረስ በሰውነታችን ውስጥ እንዳይመቸውና እንዳይስፋፋ የሚያደርጉ ናቸው
- የመከላከል አቅምን የሚያረጋጉ መድሀኒቶች (ከባድ የኮቪድ-19 ታማሚዎች የሚጎዱት የመከላከል ስርአታቸው ስለሚደናገጥና እራሱን በራሱ ስለሚያጠቃ ነው)
- ከቫይረሱ ካገገሙ ወይም ከታማሚው የሚወሰዱ ወይም ላብራቶሪ ውስጥ የሚሰሩ ቫይረሱን የሚያጠቁ አንቶቦዲዎች
እስካሁን ሙከራ ከተደረገባቸው ሁሉም መድሀኒቶች መካከል 'ስቴሮይዶች' ብቻ ሕይወት ማትረፍ እንደሚችሉ የተረጋገጠ ሲሆን ይህ ግኝትም የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት እንደ ትልቅ ስኬት ተወስዷል።
የዩኬው ሙከራ 'ዴክሳሜታዞን' የተባለው የስቴሮይድ አይነት በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሊከሰት የሚችልን ሞት በእጅጉ መቀነስ እንደቻለ ያሳየ ሲሆን በመተንፈሻ መሳሪያ ከሚረዱ ታማሚዎች መካከል አንድ ሶስተኛዎቹን ሕይወትም ማትረፍ ችሏል።
በተጨማሪም በዚህ መድሀኒት ብቻ በኦክስጅን ከሚረዱ ታማሚዎች ደግሞ አንድ አምስተኛውን ሕይወት ማትረፍ ተችሏል።
በቅርቡ በተገኘ ሌላ መረጃ ደግሞ ሌላኛው የስቴሮይድ አይነት ፤ሃይድሮኮርቲሶን' ከዴክሳሜታዞን ያልተናነስ ውጤታማነት እንዳለው ማረጋገጥ መቻሉን ባለሙያዎቹ ገልጸዋል።
ነገር ግን እነዚህ መድሀኒቶች ቀለል ያለ ምልክት የሚያሳዩ የኮቪድ-19 ታማሚዎች ላይ እምብዛም አይሰሩም።
በኮሮናቫይረስ የተጠቁ ታማሚዎችን ለማከም በጥቅም ላይ እየዋሉ ከሚገኙት መድሀኒቶች መካከል አንዱ ሆነው 'ሬምደስቪር' ነው። መድሃኒቱ በዋነኛነት የሚመረተውና ጥቅም ላይ የሚውለው ኢቦላን ለማከም ነው።
ከ1ሺህ በላይ ሰዎችን ባሳተፈና በመድሃኒቱ ላይ በተደረገ ክሊኒካዊ ሙከራ ላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ለ15 ቀናት ያሳዩት የነበረውን የሕመም ምልክት ወደ 11 ቀናት ዝቅ እንደሚያደርገው ተረጋግጧል።
ነገር ግን አሜሪካ ሁሉንም ለማለት በሚያስደፍር መልኩ አብዛኛውን መድሀኒት ገዝታዋለች። ጊሊያድ የተባለው የመድሃኒቱ አምራችም ቢሆን ለደቡብ ኮሪያ እርዳታ አድርጓል።
የኮሮናቫይረስን ለማከም በጥቅም ላይ መዋል አለባቸው ተብለው በተደጋጋሚ ሲነሱ የነበሩት ሌሎቹ መድሃኒቶች ደግሞ ለኤችአይቪ ኤድስ ታማሚዎች የሚሰጡት 'ሎፒናቪር' እና ሪቶናቪር' የተባሉት ናቸው።
ነገር ግን የዩኬው ጥናት ማረጋገጥ እንደቻለው መድሃኒቶቹ በኮሮረናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ለማከምም ሆነ ለማሻል ምንም አይነት አቅም እንደሌላቸው በማረጋገጥ ከሙከራ ስራው አስወጥቷቸዋል።
የወባ መድሀኒቶችም ቢሆኑ በስፋት ለኮሮረናቫይረስ ታማሚዎች ቢሰጡ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተነግሯል። ነገር ግን አሁንም ቢሆን ይህንን በላብራቶሪ ሙከራ ማረጋገጥ አልተቻለም።
ለወባ ህክምና ከሚውሉት በተደጋጋሚ ስማቸው የሚጠራው 'ክሎሮኪን' እና 'ሃይድሮክሎሮኪን' የተባሉት መድሀኒቶች ናቸው።
መድሃኒቶቹ ኮሮረናቫይረስን ለማከም ብቁ መሆናቸውን በርካቶች ሲናገሩ ነበር። ለዚህ የመጀመሪያው ምክንያት ደግሞ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መድሀኒቱ ፍቱን እንደሆነ መናገራቸው ነው።
ነገር ግን የዩኬው የምርምር ውጤት የሚያሳየው ሌላ ነው። ሃይድሮክሲክሎሮኪን የተባለው መድሀኒት ለኮቪድ19 ህክምና መዋል እንደማይችል ጥናቱ ያሳየ ሲሆን የዓለም ጤና ድርጅትም ቢሆን መድሀኒቱን ከሙከራ ስርአቱ አስወጥቶታል።
ባሳለፍነው ወር ደግሞ የአሜሪካ ምግብና መድሃኃኒት አስተዳደር የደም ፕላዝማ ለኮሮናቫይረስ ታማሚዎች ድንገተኛ ሕክምና እንዲውል ፈቃድ ሰጥቷል።
አንድ ሰው በኮሮናቫይረስ ሲያዝ የተፈጥሮ በሽታን የመከላከያ ሥርዓቱ በሽታን አምጪ ተህዋስያን የመከላከያ ዘዴን ያዘጋጃል፤ ይህም ቫይረሱን በማጥቃት ወደ በሽታ እንዳይሸጋገር ያደርጋል።
ይህ ሂደትም በአንድ ወር ውስጥ የሚፈጠር ሲሆን ፕላዝማ በተባለውና በደም ውስጥ ባለው ፈሳሽ ክፍል ውስጥ የሚገኝ ነው።
ይህንን ፕላዝማ በኮቪድ-19 በጠና ለታመሙ ሰዎች በመስጠት ከቫይረሱ ጋር ፍልሚያ የገጠመውን የራሳቸውን ተፈጥሯዊ በሽታን የመከላከያ ሥርዓት በማጠናከር ከበሽታው እንዲያገግሙ ለማገዝ የሚያስችል ነው።
በመሆኑም ሕክምናው ከበሽታው ካገገሙ ሰዎች ከተወሰደና በበሽታ መከላከል አቅም [አንቲ ቦዲ] የበለፀገውን ይህን የደም ፕላዝማ ይጠቀማል።
ይህ ሕክምና ቀደም ብሎ በአሜሪካ ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች ላይ ጥቅም ላይ ውሏል። ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም ሕክምናው 35 በመቶ ሞት ሊቀንስ እንደሚችል ተናግረው ነበር።
የኮሮናቫይረስን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ክትባት፣ በቂ የሚባሉ ሰዎች ቫይረሱን መቋቋም የመቻል ተፈጥሯዊ መከላከያ ማዳበርና በዘላቂነት የግለሰቦችና የማህበረሰብ ባህሪ መቀየር እንደ አማራጭ የተቀመጡ ናቸው።
ዓለም የኮሮናቫይረስ ክትባት ላይ ለመድረስ ቢያንስ ከአመት እስከ ዓመት ተኩል የሚሆን ጊዜ ይቀረዋል።
ክትባቱ ቢያንስ 60 በመቶ ለሚሆኑ ሰዎች ተሰጥቶ እነዚህ ሰዎች ቫይረሱን የመከላከል አቅም አዳብረው ለቫይረሱ ተጋልጠው እንኳ የማይታመሙ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
በያዝነው ወር ደግሞ የሩስያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን የኮቪድ-19 ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ፍቃድ ማግኘቱን ተናግረዋል።
በአገራቸው ላለፉት ሁለት ወራት በሰዎች ላይ ሙከራ እየተደረገበት የነበረው ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል መፈቀዱንም ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።
ክትባቱ አስፈላጊውን የምርመራ ሂደት ማለፉን የገለጹት ፑቲን፤ ልጃቸው ክትባቱን እየወሰደች እንደምትገኝም ተናግረዋል።
ጥቅምት ላይ ክትባቱን በጅምላ የመስጠት እቅድ እንዳለ የአገሪቱ አመራሮች ቢናገሩም፤ ባለሙያዎች የሩስያ የክትባት ምርምር እየሄደ ያለበት ፍጥነት ላይ ጥያቄ አንስተዋል።
የሩስያ ክትባት ድርጅቱ በሦስተኛ ደረጃ ሙከራ ላይ ካስቀመጣቸው ክትባቶች አንዱ አይደለም። እነዚህ ክትባቶች በሰዎች ላይ ተሞክረው ተጨማሪ ምርምር መካሄድ አለበት።
ፕሬዘዳንት ፑቲን ግን፤ በሞስኮው ጋማሊያ ተቋም ውስጥ የተሠራው ክትባት ቫይረሱን “በዘላቂነት ለመከላከል የሚያስችል” ነው ብለዋል።
የሩስያ የጤና ሚንስትር ሚካኤሊ ሙራሽኮ፤ ክትባቱ “በጣም ውጤታማና ደህንነቱ የሚያስተማምን” ነው ብለዋል። ክትባቱ የሰው ልጆች ኮቪድ-19ን ድል የሚነሱበት እርምጃ እንደሆነም መናገራቸው አይዘነጋም።












