ፍርድ ቤት የአቶ ልደቱን መዝገብ ቢዘጋም አሁንም እስር ላይ ናቸው

ሁከት በማስተባበርና በመደገፍ ተጠርጥረው በፖሊስ ተይዘው የቆዩትን የአቶ ልደቱ አያሌውን ጉዳይ ሲመለከት የነበረው ፍርድ ቤት ፖሊስ ያቀረበውን የተጨማሪ ጊዜ ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የምርመራ መዝገቡን ቢዘጋውም እስር ላይ መሆናቸውን የኢዴፓ ፕሬዝዳንት አቶ አዳነ ታደሰ ለቢቢሲ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው ዛሬ ጠዋት ነበር በቀጠሯቸው ቢሾፍቱ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት የቀረቡት።
በዛሬው ችሎት አቶ ልደቱ አያሌው ላይ ፖሊስ ሲያካሂድ የቆየውን ምርመራ ማጠናቀቁን ገልጾ ዐቃቤ ህግ ክስ እስከመሰርት ድረስ የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ቢጠይቅም ፍርድ ቤቱ የፖሊስን ጥያቄ የህግ አግባብነት እንደሌለው ጠቅሶ ሳይቀበለው መቅረቱን አቶ አዳነ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ፍርድ ቤቱ የፖሊስ የምርመራ መዝገብ መዘጋቱን ገልጾ አቶ ልደቱ አያሌው በሌላ መዝገብ የዋስትና ጥያቄያቸውን እንዲያቀርቡ ማዘዙን ጠቅሰዋል።
አቶ አዳነ እንዳሉት፤ ችሎቱ ፖሊስ እስካሁን አለኝ ያለውን የምርመራ ውጤትን ቢያቀርብም ፍርድ ቤቱ የቀረበው ማስረጃ አቶ ልደቱን አያስከስስም ብሎ መዝገቡን ዘግቷል ብለዋል።
ችሎቱ አቶ ልደቱን የሚያስከስስ ማስረጃ አለማገኘቱን ገልጾ ጉዳዩን ቢቋጨውም፣ አቶ ልደቱ እስካሁን [እስከ ዛሬ ቀትር ድረስ] እንዳልተለቀቁ ተናግረው፤ ስለዚህም አባላቸው ከእስር እንዲወጡ ነገ ሁለት ማመልከቻዎችን ሊያስገቡ እንዳሰቡ አቶ አዳነ አክለዋል።
"አንደኛው የዋስ መብት የሚጠየቅበት ማመልከቻ ነው። ሌላኛው ደግሞ አካልን ነጻ የማውጣት ክስም እንመሰርታለን” ብለዋል።
አቶ ልደቱ በፍርደ ቤት ነፃ ከተባሉ በኋላ ለምን ከእስር እንደማይለቀቁ ጠይቀው፤ ከፍርድ ቤት እንዲሁም ከፖሊስ ያገኙት ምላሽ፤ “አሠራራችን ነው። የዋስትና ማመልከቻ አስገቡ” መባላቸውንም አቶ አዳነ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
"የፍትሕ ሥርዓቱ የምናውቀው ስለሆነ ነገ ከነገ ወዲያ ምን እንደሚከሰት አናውቅም። በፍርድ ቤት ይህ አይነት ውሳኔ ቢወሰንም ፖሊስ አልለቀቃቸውም። የዋስትና ማመልከቻ ካልቀረበ እንደማይለቃቸውም ገልጿል። ይሄ አስፈጻሚው ከፍርድ ቤት የበለጠ ጡንቻ እንዳለው ያሳያል” ብለዋል የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ አዳነ።
የልብ ህመም ያለባቸው አቶ ልደቱ "ደህና ነኝ ልል አልችልም። እርግጠኛ የሚሆነው ቀዶ ሕክምና ያደረግኩበትን ዓመታዊ ክትትል ሳደርግ ነው" ብለው ስለ ጤና ሁኔታቸው እንደነገሯቸውም አያይዘው ገልጸዋል።
አቶ ልደቱ ከአንድ ወር በፊት በፌደራል ፖሊስ ተይዘው ለኦሮሚያ ፖሊስ ተላልፈው ከተሰጡ በኋላ መኖሪያ ቤታቸው በሚገኝበት የቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ በእስር ላይ ይገኛሉ።
አቶ ልደቱ ለእስር የተዳረጉት ከሁለት ወራት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ የተከሰተውን የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ከተከሰተው ሁከት ጋር በተያያዘ ቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ ሁከቱን በማነሳሳትና በመደገፍ ተጠርጥረው እንደተያዙ ተገልጾ ነበር።














