ልዩ ፍላጎት፡ የደቡብ አፍሪካ ፖሊሶች የአዕምሮ እድገት ውስንነት ባለበት ታዳጊ ግድያ በቁጥጥር ሥር ዋሉ

የ16 ዓመት ታዳጊን ተኩሰው 'በመግደል' ሁለት የደቡብ አፍሪካ ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለፀ።

ናታኔል ጁሊየስ የተባለው ታዳጊ 'ዳውንስ ሲንድረም' [የአዕምሮ እድገት ውስንነት] የነበረበት ነው ተብሏል።

ታዳጊው በጆሃንስበርግ ኤልዶራዶ ፓርክ የመኖሪያ መንደር የተገደለው ብስኩት ለመግዛት በወጣበት እንደሆነም የሟች ቤተሰቦች ተናግረዋል።

ልጃቸው የተገደለውም ባለበት የጤና እክል ምክንያት ፖሊስ ለጠየቀው ጥያቄ መልስ መስጠት ባለመቻሉ ነው ብለዋል ቤተሰቦቹ።

ፖሊስ መጀመሪያ ላይ ታዳጊው በፖሊሶች እና በወንበዴዎች መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ተሳትፎ እንደነበር ተናግሮ ነበር።

ይሁን እንጂ ገለልተኛ የሆነው የፖሊስ መርማሪ ዳሬክቶሬት በእጁ የገባውን መረጃ በጥንቃቄ ከተመለከተ በኋላ ፖሊሶቹን ለማሰር እንደወሰነ ተናግሯል።

ፖሊሶቹ በግድያ ወንጀል እንደሚከሰሱ የተገለፀ ሲሆን፤ "በፍርድ ሒደቱ ሊረቱ እንደሚችሉ" በፖሊስ የተፈፀሙ ከባድ ወንጀሎችን የሚመረምረው ይኸው ገለልተኛ ተቋም አስታውቋል።

የታዳጊውን ግድያ ተከትሎ በአገሪቷ ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር።

ተቃውሞው የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ ሕዝቡ እንዲረጋጋ ወጥተው እስከመጠየቅ ያደረሰ ነበር።

ዳውንስ ሲንድረም ምንድን ነው?

'ዳውንስ ሲንድረም' የተባለው የአዕምሮ እድገት ውስንነት ስያሜውን ያገኘው በመጀመሪያ የበሽታውን ዓይነት በለዩት ዶክተር ጆን ላንግዶን ዳውን ስም ነው።

ለዚህ የጤና እክል የተዳረጉ ሰዎች ከውልደት ጀምሮ አካላዊና አዕምሯዊ እድገት ውስንነት ይታይባቸዋል።

ይህ የጤና እክል በአብዛኛው የሚከሰተው በተዛባ የዘረ መል ችግር ምክንያት ነው። አንድ ጤነኛ ሰው 21 ክሮሞዞሞች ሁለት እጥፍ [48] ያለው ሲሆን ለዳውንስ ሲንድረም የሚጋለጡት ሦስት እጥፍ በሚሆንበት ጊዜ ነው።

ዳውንስ ሲንድረም ከዘር፣ ብሔር፣ ከኢኮኖሚ ደረጃ ወይም ሃይማኖት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም።