ቤይሩት ፍንዳታ፡ በአደጋው 15 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ውድመት መድረሱ ተገለፀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዓለም መሪዎች ከአምስት ቀናት በፊት በከባድ ፍንዳታ ለተመታችው የሊባኖሷ መዲና ቤይሩት እርዳታ ለማሰባሰብ ዛሬ ጉባኤ እንደሚያካሂዱ ተገለፀ።
ይህ በበይነ መረብ (ቨርቹዋል) የሚካሄደው ስብሰባ በፈረንሳይና በተባበሩት መንግሥታት የተዘጋጀ ሲሆን ስምንት ሰዓት ላይ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።
የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ለአገሪቷ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ለማሰባሰብ ማስተባበር እንደሚፈልጉ የተናገሩት ሐሙስ ዕለት ቤይሩትን በጎበኙበት ወቅት ነበር።
ዛሬ የሚካሄደው ጉባኤ የሊባኖስ ዋና ዋና ዓለም አቀፍ አጋሮችን ለማሰባሰብና ከዓለም አቀፍ ማሕበረሰቡ አስቸኳይ ድጋፍ ለማሰባሰብ ያለመ መሆኑም ከፕሬዚዳንቱ ቢሮ የወጣው መግለጫ አመልክቷል።
በጉባኤው ላይ የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት ተወካዮች ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ግብፅ፣ ጆርዳን እና ዩናይትድ ኪንግደም የሚሳተፉ ሲሆን ሌሎች በርካቶችም ተጋብዘዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቤይሩት ስለተከሰተው ድንገተኛ አደጋ ከፕሬዚደንት ኢማኑኤል ጋር ተወያይተው እንደነበር ገልፀው፤ በስብሰባው ላይ ለመሳተፍ እንዳቀዱ በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።
በርካታ አገራት ቤይሩትን ለመርዳት በሚሊየን ዶላሮች የሚገመት እርዳታ፣ መርከቦች፣ የጤና ባለሙያዎችንና ቁሳቁሶችን ልከዋል።
ይሁን እንጂ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአገሪቷ ከፍተኛ ቀውስ ሊያጋጥም እንደሚችል በማስጠንቀቅ ተጨማሪ እርዳታ እንደሚያስፈልግ ጥሪ አቅርቧል።
በርካታ ቤቶች የውሃና የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተቋረጠባቸው ሲሆን የምግብ ፍጆታ እጥረት እንደሚያጋጥምም ስጋት አለ።
ከዚህም ባሻገር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሥርጭት እየጨመረ ሲሆን ይህም በፍንዳታው በተጎዱ ሰዎች በተጨናነቁት ሆስፒታሎች ላይ ተጨማሪ ጫና ፈጥሯል።
የዩኒሴፍ ቃል አቀባይ ማሪክሴ ሜርካዶ አርብ ዕለት ጀኔቫ ለሚገኙ ጋዜጠኞች "አፋጣኝና ከፍተኛ ድጋፍ" እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የሊባኖስ ባለሥልጣናት 2 ሺህ ቶን የሚመዝን አሞኒየም ናይትሬት ደህንነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ ለስድስት ዓመታት ተከማችቶ በነበረበት መጋዘን በተከሰተው ፍንዳታ፤ 15 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ጉዳት እንደደረሰ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
በፍንዳታው ቢያንስ 158 ሰዎች የሞቱ ሲሆን 5 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት አጋጥሟቸዋል፤ 300 ሺህ የሚሆኑት ቤት አልባ ሆነዋል።
ይህንንም ተከትሎ ቅዳሜ ዕለት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መንግሥትን ለመቃወም አደባባይ የወጡ ሲሆን፤ ፖሊስም በመንግሥት መስሪያ ቤቶች ላይ ድንጋይ በመወርወር ተቃውሟቸውን ሲገልፁ በነበሩት ላይ አስለቃሽ ጭስ ረጭቷል።
የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃሰን ዲያብም ከዚህ ቀውስ ለመውጣት ቀድሞ ከተያዘው ጊዜ ቀድሞ ምርጫ እንዲካሄድ ሊጠይቁ እንደሚችሉ የተገለፀ ሲሆን በጉዳዩ ላይም ካቢኔው ሰኞ ውይይት ያደርግበታል ተብሏል።
ቀደም ሲል በከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ የገባችው ሊባኖስ፤ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመዋጋት እየተጣጣረች ባለበት ሰዓት ነው ፍንዳታው ያጋጠማት።
በአገሪቷ ያጋጠመውን የኢኮኖሚ ቀውስና የመገበያያ ገንዘቧ ዋጋ መውደቅ ተከትሎ ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር።












