ሕዝብ፡ የዓለም የሕዝብ ቁጥር ቢቀንስ ምን ሊፈጠር ይችላል?

ህጻን የያዙ አዛውንት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የወሊድ መጠን እየቀነሰ ይሄዳል ማለት በምዕተ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የበርካታ አገሮች የሕዝብ ቁጥር ያንሳል ማለት ነው።

ጥቂት ሕዝብ እንዲሁም አረጋውያን የሚበዙባቸው አገሮች መፈጠራቸውም አይቀርም። ተከታዮቹ ስድስት ነጥቦች ከዓለም ሕዝብ ቁጥር መቀነስ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ናቸው።

1. ለድሃ አገራት መልካም ዜና ነው

የወሊድ ቁጥር እና የምጣኔ ሀብት እድገት ጎን ለጎን ይሄዳሉ።

ሴቶች በአማካይ ጥቂት ልጆች ብቻ የሚወልዱት፤ በተሻለ ሁኔታ ትምህርትና ሥራ ሲያገኙ፣ የእርግዝና መቆጣጠሪያ ተደራሽ ሲሆን፣ ማስወረድን የሚከለክል ሕግ ሲላላ እንዲሁም የጨቅላዎች ሞት ሲቀንስ ነው።

አነስተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች የወሊድ መጠን ሲቀንስ፤ በርካቶች የተሻለ ሕይወት የማግኘት እድላቸው ይሰፋል።

ጥቂት ልጆች ብቻ ሲወለዱ፤ እያንዳንዳቸው የተሻለ ትምህርትና የጤና አገልግሎትም ያገኛሉ።

ባለፉት ዓመታት የወሊድ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰባቸው አገሮች ግን እምብዛም አይጠቀሙም። በእነዚህ አገሮች አረጋውያን የሚንከባከባቸው ያጣሉ። የምርታማ ወጣቶች ቁጥርም ይቀንሳል።

2. ብዙዎች ጡረታ መውጣትን በጉጉት መጠበቅ ይጀምራሉ

ብዙዎች ጡረታ መውጣትን በጉጉት የሚጠባበቁበት ዓለም ይፈጠራል። በሥራ ላይ የሚያሳልፏቸው ዓመታት ቁጥርም ይጨምራል።

የአረጋውያን ቁጥር ሲጨምር የጤና ሥርዓት ችግር ውስጥ ይገባል የሚል ፍርሀት ቢኖርም፤ ሁሉም አዛውንቶች ስለማይታመሙ ያን ያህል አስጊ ላይሆን ይችላል።

ዓለም ላይ የሰዎች እድሜ ከመጨመሩ ጎን ለጎን ጤናማ ሆነው የሚያረጁ ሰዎች ቁጥርም ከፍ እያለ መጥቷል።

በኦክስፎርድ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሣራ ሀርፐር እንደሚሉት፤ የአረጋውያን ቁጥር ይጨምራል የሚለው ስጋት አንዳንድ እውነታዎችን ከግምት ማስገባት አለበት።

“ከአስር ዓመታት ወዲህ የአረጋውያን የጤና ሁኔታ እየተሻሻለ መጥቷል። ስለዚህም አረጋውያን ጤናማ ሆነው መንቀሳቀስ ይችላሉ” ይላሉ።

በአሁን ወቅት የሚወለዱ ልጆች ከ20 ዓመታት በፊት ከተወለዱት ጋር ሲነጻጸሩ፤ ለአምስት ተጨማሪ ዓመታት ጥሩ ሕክምና ያገኛሉ።

በእርግጥ ይህ በሶርያ የሚወለዱ ሕፃናትን አይጨምርም።

ሁለተኛው ምዕተ ዓመት ከተጀመረ ወዲህ በሩዋንዳ የሚወለዱ ልጆች 22 ተጨማሪ ዓመታት መኖር ጀምረዋል።

በገቢ ባደጉት እንደ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን እና አሜሪካ ያሉት አገራት፤ የዜጎች ዕድሜ ከአንድ እስከ ሦስት ዓመት ጨምሯል።

3. መንግሥታትድንበራቸውንመክፈትይጠበቅባቸዋል

ሦስተኛው ነጥብ የስደተኞች ጉዳይ ነው።

የወሊድ መጠን በመቀነሱ ሳቢያ አነስተኛ ወጣት ያላቸው አገራት፤ የሌሎች አገሮች ወጣት ተወላጆችን ወደ ግዛታቸው ለማስገባት መሞከር አለባቸው።

ይህም ዓለም ላይ ያሉ ዘሮች እንዲሁም ባህላቸውም እንዲዋሀድ መንገድ ይፈጥራል።

4. ቤተሰብን የመንከባከብ ጉዳይ

በስካንድኔቪያን አገሮች መንግሥት ልጅ መውለድን ያበረታታል። ለወላድ እናቶች የሚሰጠው ጊዜና ለልጅ እንክብካቤ የሚደረገው ድጋፍ ሴቶች ከተጠበቀው በላይ እንዲወልዱ አበረታቷል።

ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የሚሠሩት ዶ/ር ሃና ሪቺ እንደሚሉት፤ የሀብታም አገራት መንግሥታት ማበረታቻ የወሊድ ቁጥርን ይጨምራል።

በድሃ አገራት ሴቶች ከሚፈልጉት በላይ ልጆች ሊወልዱ ይችላሉ። በሌላ በኩል ኑሮ ውድ በሆነባቸው አገሮች ልጆችን ማሳደግ ከባድ ስለሆነ ጥንዶች ብዙ አይወልዱም።

ይህን ተከትሎ መንግሥታት ሰዎች ጡረታ የሚወጡበትን እድሜ ሊያራዝሙ ይችላሉ።

ፕሮፌሰር ሣራ እንደሚሉት፤ ቤተሰብን ለመንከባከብ ሰፊ ጊዜ ተሰጥቶ፤ የሥራ ዘመን ግን እንዲጨመር በመንግሥታት ሊወሰንም ይችላል።

5. አሳሳቢው የሥራ ጉዳይ

በለንደን የምጣኔ ሀብት ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ቲዚና ሊዎን እንደሚሉት፤ አረጋውያን ምንም ያህል ጠንካራ ቢሆኑም ወደ እድሜ ዘመናቸው መገባደጃ አካባቢ አጋዥ ያስፈልጋቸዋል።

የአረጋውያን ቁጥር ከፍተኛ በሆነባቸው አገሮች የጤና እንዲሁም የማኅበረሰባዊ መዋቅር ቀውስ ሊገጥም እንደሚችልም ባለሙያው ያሳስባሉ።

ስለዚህም ከአሁኑ ሠራተኞችን በዘርፉ ማሰልጠን መጀመር እንዳለበት ዶ/ር ቲዚና ያስረዳሉ።

“ለወደፊቱ የሕፃናት ወይም የማህጸን ሀኪሞች ብዙም ላያስፈልጉን ይችላሉ” ይላሉ።

6. ተፈጥሮልታገግምትችላለች

የሕዝብ ቁጥር ሲቀንስ ተፈጥሮ እንደምታገግም ፕ/ር ሣራ ያስረዳሉ።

ዶ/ር ሃና በበኩላቸው ከሕዝብ ቁጥር ይልቅ የምጣኔ ሀብት እድገት ተፈጥሮ ላይ ጫና እንደሚያሳድር ያምናሉ።

አገራት በምጣኔ ሀብት በልጽገው ተፈጥሮን የሚበዘብዙ ከሆነ የሕዝብ ቁጥር መቀነሱ ለውጥ አያመጣም።

ባለፉት አስርታት የምጣኔ ሀብት እድገት እና የአካባቢ ብክለት ቀጥተኛ ግንኙነት ነበራቸው። አሁን ግን ሀብታም አገሮች የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀታቸውን ቀንሰው ቴክኖሎጂ ላይ ገንዘባቸውን እያፈሰሱ ነው።