ዚምባብዌ የአሜሪካ አምባሳደርን አገሪቷን አበጣብጠዋል በሚል አባርራለሁ አለች

የፎቶው ባለመብት, US EMBASSY
የዚምባብዌ ገዢ ፓርቲ ዛኑ ፒኤፍ በባለፈው ሳምንት በአገሪቱ የተደረገውን የተቃውሞ ሰልፍ ድጋፍ በማድረግ የአሜሪካ ኤምባሲን ወንጅለዋል። አምባሳደሩን ከአገር አባርራለሁ በማለትም አስፈራርተዋል።
ምንም እንኳን ተቃውሞው በአገሪቱ ውስጥ የተንሰራፋውን ሙስና ለመቃውም ነው ቢባልም የፓርቲው ቃለ አቀባይ ፓትሪክ ቺናማሳ እንዳሉት መንግሥትን ለመገልበጥ የተደረገ ነው ብለዋል። ተቃዋሚዎቹ በዚህ ተግባራቸው የሚቀጥሉም ከሆነ ተመጣጣኝ ኃይል መንግሥት እንደሚጠቀምም አስጠንቅዋዋል።
ቃለ አቀባዩ አክለውም የአሜሪካ አምባሳደር ብሪያን ኒኮልስንም የዱርዬ ተግባር ነው ያሳዩት በማለትም ወርፈዋቸዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነትም ለመበላሸቱም ማሳያ ነው ተብሏል። አሜሪካ በዚምባብዌ ውስጥ ያለው ሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋር በተያያዘ የኢኮኖሚ ዕቀባ መጣሏ የሚታወስ ነው።
ከዚህ ቀደምም በአገሪቱ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አገሪቷን ለማበጣበጥ ይሰራል መባሉን ውንጀላ ነው በማለት ክዷል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በአገሪቷ ውስጥ ጭማሬ ማሳየቱን ተከትሎ መንግሥት የተለያዩ መመሪያዎችን አስተላልፏል።
እነዚህ መመሪያዎችንም በተመለከተ መንግሥት ወረርሽኙን በመጠቀም መሰረታዊ የሚባሉ መብቶችን እየጣሰ ነው በማለት ተቃዋሚዎች እየወነጀሉ ነው።
በባለፈው ሳምንት አንድ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ሰልፍ በማስተባበር በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ጋዜጠኛም እንዲሁም በተቃውሞ ሰልፉ በመሳተፍ ታስሯል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ቢሮ ወረርሽኙ ነፃነትን ለመገደብ እንደ ሽፋን ሊጠቀሙበት አይገባም ብለዋል።












