ሩስያ ሕዋ ላይ የጦር መሣሪያ ሞክራለች ሲሉ አሜሪካ እና እንግሊዝ ወቀሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዩናይትድ ስቴትስና ዩናይትድ ኪንግደም፤ ሩስያ ሕዋ ላይ የጦር መሣሪያ ባሕሪ ያለው ነገር ሞክራለች ሲሉ ወቅሰዋል።
ሁለቱ ሃገራት መሣሪያው ሕዋ ላይ ያሉ ሳተላይቶችን ለማውደም ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል የሚል ስጋት አላቸው። የአሜሪካ ሃገር ውስጥ ጉዳዮች መሥሪያ ቤት 'ሕዋ ላይ የታየው ፀረ-ሳተላይት መሣሪያ' አሳስቦኛል ብሏል።
የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር ሕዋ ላይ ያሉ የሩስያ ንብረቶች ላይ ምርመራ የሚያካሂድ አዲስ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ሊያውል መሆኑን አሳውቆ ነበር።
አሜሪካ ሕዋ ላይ ይንቀሳቀሳል የተባለው የሩስያ ቴክኖሎጂ ላይ ጥርጣሬ ገብቶኛል ካለች ዘግየት ብትልም ዩናይት ኪንግደም ግን ቅሬታዋን ስታሰማ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
የዩናይት ኪንግደም ሕዋ ዳይሬክተር ሃርቪ ስሚዝ፤ ሩስያ ሕዋ ላይ እያሳየችው ያለው ባሕሪ እንዳሰጋቸው አልሸሸጉም።
"የሩስያ ድርጊት ሰላማዊውን የሕዋ ምህዳር የሚያውክ ነው። አልፎም ስብርባሪዎች ዓለም የሚጠቅማባቸው ሳተላይቶች አደጋ ሊያደርሱ ይችላሉ። ሩስያ ኃላፊነት ሊሰማት ይገባል።"
ሩስያ፣ አሜሪካ፣ ዩኬ እና ቻይናን ጨምሮ ሌሎች ከ100 በላይ ሃገራት ሕዋን በሰላማዊ መንገድ በጋራ ለመጠቀም ስምምነት ገብተዋል።
ስምምነቱ የጦር መሣሪያዎችን ሕዋ ላይ መጠቀም እንደማይቻል ያትታል።
የአሜሪካ ሕዋ ቁጥጥር ኃላፊ ጄኔራል ጄይ ሬይመንድ፤ ሩስያ ሕዋ ላይ ፀረ-ሳተላይት መሣሪያ መሞከሯን የሚያሳይ ማስረጃ አለን ይላሉ።
ሩስያ ከሳተለይት ጋር በተያያዘ ከአሜሪካ ወቀሳ ሲደርስባት ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ባለፈው የካቲት ሁለት የሩስያ ሳተላይቶች በአንድ የአሜሪካ ሳተላይት ዙሪያ ሲንያዣብቡ ነበር ስትል አሜሪካ መክሰሷ አይዘነጋም። ባለፈው ጥር ደግሞ ሩስያ ከመሬት ሕዋ ላይ ያለን ሳተላይት ሊያጠቃ የሚችል መሣሪያ ሙከራ አድርጋ ነበር።
ባለፉት አስር ዓመታት ፀረ-ሳተላይት መሣሪያ ሙከራ ያደረጉ ሃገራት አራት ብቻ ናቸው። እኒህም ሩስያ፣ አሜሪካ፣ ካናዳ እንደ ሕንድ ናቸው።
ነገር ግን ሩስያ ሳተላይትን የሚያወድም ሳተላይት ሠርታለች ተብላ ነው የምትወቀሰው።
ብዙዎች ሕዋ ቀጣዩ የጦርነት ቀጣና እየሆነ መጥቷል ይላሉ። ይህም የሆነበት ምክንያት ምህዳሩ ለመረጃ መሰብሰቢያ፣ ለግንኙነት፣ ምርምርና ቅድመ-ማስጠንቀቂያ እየዋለ በመሆኑ ነው።














