በፕሪንስተን ዩኒቨርስቲ የውድሮው ዊልሰን ስም በ'ዘረኝነት ምክንያት' ከህንፃዎቹ ሊወገድ ነው

ፕሪንስተን ዩኒቨርስቲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፕሪንስተን ዩኒቨርስቲ የቀድሞውን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ውድሮው ዊልሰን ስም በግቢው ውስጥ ከሚገኙ ህንፃዎች እንደሚያስወግድ አሳውቋል። ዩኒቨርስቲው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ፕሬዚዳንቱ ዘረኛ በመሆናቸውና ፖሊሲያቸውም ዘረኝነት የተንሰራፋበት በመሆኑ ነው ተብሏል።

በነጭ ፖሊስ ተደፍቆ የተገደለውን ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ተከትሎ በርካታ ተቃውሞዎች ተቀጣጥለዋል እንዲሁም የባርያ ፈንጋዮች፣ ዘረኞችና ጨፍጫፊዎች ሃውልትም እየተገረሰሰ ነው።

ውድሮው ዊልሰን በጎርጎሳውያኑ 1913- 1921 አሜሪካን የመሩ 28ኛው ፕሬዚዳንት ሲሆኑ ከተባበሩት መንግሥታት በፊት የነበረውን ሊግ ኦፍ ኔሽንስ ለመመስረቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል።

ሆኖም በተቃራኒው ከነጭ ህዝብ ውጭ ያለው በተለይ ጥቁሮች በፖሊሲ ደረጃ እንዲገለሉና የተለያየ መድልዎች እንዲፈፀምባቸው ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

በፕሪንስተንም ዩኒቨርስቲ በፕሬዚዳንትነት ባገለገሉበት ወቅት ጥቁር ተማሪዎች በዩኒቨርስቲው ገብተው እንዳይማሩ ከልክለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ጥቁር አሜሪካውያንን በማቃጠልና በመስቀል በጭካኔ በመግደል የሚታወቀው የኬኬኬ (ኩ ክሉክስ ክላን) የተባለውንም ፅንፈኛ ቡድን ድጋፍ ሲሰጡ ተሰምተዋል።

የዩኒቨርስቲውን ውሳኔ አስመልክቶም የፕሪንስተን ፕሬዚዳንት ክርስቶፈር ኤይስግሩበር በሰጡት መግለጫ "በጊዜውም ቢሆን እንኳን ቢታይ፣ ዊልሰን ከፍተኛ ዘረኝነት የተፀናወተው ነው " ብለዋል።

በዚህም መሰረት የዩኒቨርስቲው ቦርድ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሰዎችን እኩል ካለማየታቸውና ዘረኛ ፖሊሲም ከመከተላቸው አንፃር ህዝብ የሚገለገልበት ዩኒቨርስቲ ህንፃዎች በስማቸው መጠራቱ ተገቢ አይደለም ወደሚል ውሳኔ መድረሳቸውም ተገልጿል።

28ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ውድሮው ዊልሰን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከዚህም በተጨማሪ በሳቸው ስም ተሰይሞ የነበረውም የፐብሊክ ፖሊሲ የትምህርት ክፍል ተቀይሮ 'ፕሪንስተን ስኩል ኦፍ ፐብሊክ ኤንድ ኢንተርናሽናል አፌይርስ (Princeton School of Public and International Affairs) እንዲሆን ተወስኗል።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት እንዳሉት ውድሮው ዊልሰን ክብር የተሰጣቸው "ዘረኝነታቸውን ባለማወቅ ወይም ዝም ብሎ በመተው እንጂ ዘረኛ በመሆናቸው አይደለም" ብለዋል

አክለውም "ፕሪንስተን እንደ ሌሎች የአሜሪካ ተቋማት ዘረኝት እንዳልተከሰተና እንዳልተፈጠረ እንዲሁም ጥቁሮችን የሚያገልል ስርአቶችን የሚከተል ነው። ይህ መሰረታዊ ችግር ነው።" ብለዋል።

በባለፈው ወርም እንዲሁ በኒውጀርሲ የሚገኘው ሞንማውዝ ዩኒቨርስቲ የፕሬዚዳንት ውድሮው ዊልሰንን ስም ከህንፃዎቹ እንዲወገድ አድርጓል።

የጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ተቋማዊ ዘረኝነት እንዲቆም በርካታ ጥያቄዎችን አጭሯል።

በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ ሃገራት ባርያ የፈነገሉ፣ ሚሊዮኖችን የጨፈጨፉ ዘረኞች ሃውልትም ተገርስሷል። ነገር ግን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት እነዚህን ሃውልቶች የሚገረስሱ ተቃዋሚዎች እንዲታሰሩ የሚያዝ መመሪያ ከሰሞኑ ፈርመዋል።