ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ የደኅንነት ምስጢር ይዟል የተባለው መጽሐፍ እንዳይሰራጭ ክስ ተመሰረተ
የአሜሪካ የፍትህ ቢሮ በቀድሞው የዶናልድ ትራምፕ የደኅንነት ከፍተኛ አማካሪ ጆን ቦልተን ላይ ክስ ከፍቷል።
ክሱ ጆን ቦልተን የጻፉትና በኅትመት ላይ ያለ መጽሐፍ ታትሞ እንዳይሰራጭ ለማገድ የታሰበ ነው።
ክሱ እንደሚያስረዳው ጆን ቦልተን መጽሐፋቸው ላይ ለሕዝብ ይፋ መደረግ የሌለበት ከፍተኛ የአገር ደኅንነት ምስጢርን ይዟል።
ይህ ክስ የተከፈተው ዶናልድ ትራምፕ የቀድሞው አማካሪያቸው ጆን ቦልተንን "በወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት ሊቀርብ ይችላል" ብለው ካስጠነቀቁ በኋላ ነው።
ይህ መጽሐፍ "ዘ ሩም ዌር ኢት ሃፕንድ" የሚል ርዕስ ሲኖረው በሰኔ 23 ሊመረቅ ቀጠሮ ተይዞለታል።
መጽሐፉ ቦልተን ከእኔ ጋር ያደረገውን እያንዳንዱን የደኅንነት ጉዳይ የያዘ ነው፤ ይህ ማለት ይሄ ሰውዬ መጽሐፍ ከጻፈና ያን መጽሐፍ ካሳተመው በወንጀል መጠየቁ አይቀርለትም ብለዋል ዶናልድ ትራምፕ ሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች።
የአሜሪካ ሲቪል ሊበርቲ ዩኒየን በበኩሉ የትራምፕ አስተዳደር ይህን መጽሐፍ ለማዳፈን የሚያደርገው ሙከራ ሁሉ ከንቱ ነው ሲል ተችቷል።
የቦልተን ጠበቃ ቻርለስ ኩፐር ለተከፈተባቸው ክስ በቂ ምላሽ እያዘጋጁ እንደሆነ አረጋግጠዋል።
ባለፈው ጥር ዋይት ሀውስ ጆን ቦልተን እየጻፉት ያለው መጽሐፍ ከፍተኛ የአገር ምስጢር ስለያዘ እንዳይታተም አስጠንቅቆ ነበር። ጆን ቦልተን ግን ማስጠንቀቂያውን ቸል ብለውታል።
ይህ መጽሐፍ ይዟቸዋል ከተባሉ ምስጢሮች አንዱ ዶናልድ ትራምፕ ለዩክሬን ሊሰጥ የነበረውን ወታደራዊ የገንዘብ እርዳታ ለእራሳቸው ጥቅም ሲሉ አዘግይተዋል የሚል ነው።
ይህም ጉዳይ ፕሬዝዳንቱን አስከስሷቸው እንደነበር አይዘነጋም።
ፕሬዝዳንቱ የዩክሬን እርዳታ እንዲዘገይ ያደረጉት በምላሹ የዩክሬን መንግሥት የእርሳቸው ተፎካካሪ የሆኑት ጆ ባይደንና ልጃቸው ሀንተር በዩክሬን የሙስና ክስ ከፍቶ እንዲመረምራቸው ለማግባባት ነበር ተብሏል።
የዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ የደኅንነት አማካሪ የነበሩት ጆን ቦልተን ወደ ዋይት ሃውስ የመጡት በሚያዚያ 2018 ሲሆን በቀጣዩ ዓመት መስከረም ሥራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ቦልተን መቼ በገዛ ፈቃዱ ሥራ ለቀቀ፤ እኔ ነኝ ያባረርኩት ይላሉ።