በናይጄሪያ በቦኩ ሃራም ሳይፈጽሙት አልቀረም በተባለ ጥቃት ቢያንስ 59 ሰዎች ተገደሉ

ካርታ

በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ ጸንፈኛ ጂሃዲስቶች ሳይፈጽሙት አልቀረም በተባለ ጥቃት ቢያንስ 59 ሰዎች ተገደሉ።

ታጣቂዎች በቦርኖ ግዛት ውስጥ በምትገኝ መንደር ውስጥ በወሰዱት እርምጃ ነው ሰዎቹ የተገደሉት።

የአካባቢ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ከሆነ ጥቃቱ በነዋሪዎቹ ላይ ከተሰነዘረ በኋላ መንደሯ ሙሉ በሙሉ እንድትወድም ተደርጓል።

ኤኤፍፒ እንደዘገበው ከሆነ ጥቃቱ ከተሰነዘረበት ስፍራ ቢያንስ የ59 ሰዎች አስክሬን ተሰብስቧል። ሬውተርስ በበኩሉ 69 ሰዎች ተገድለዋል ሲል ዘግቧል።

የአካባቢው መገናኛ ብዙሃን ጨምረው እንደዘገቡት ከሆነ ጥቃቱ የተሰነዘረው የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ነው። ሬውተርስ እንደሚለው ከሆነ፤ ምንም እንኳ ለዚህ ጥቃት ኃላፊነቱን የወሰደ ቡድን ባይኖርም፤ የመንደሯ ነዋሪዎች በአካባቢው ስለሚንቀሳሱት ሚሊሻዎች መረጃ ለናይጄሪያ መንግሥት መረጃ ያቀብላሉ ተብለው በጂሃዲስቶች ይወነጀላሉ።

ኤኤፍፒ የመንደሯ ነዋሪዎች ከብቶቻቸውን ከዘራፊዎች ለመጠበቅ ሲሉ የሚሊሻው አባላት የሆኑትን ገድሏል ሲል ዘግቧል።

ምንም እንኳ ለዚህ ጥቃት ኃላፊነቱን የወሰደ አካል ባይኖርም ጂሃዲስቱ ቦኮ ሃራም በሰሜን ናይጄያ ግዛት ለሚፈጸሙ ተመሳሳይ ጥቃቶች ኃላፊነቱን ሲወስድ ቆይቷል።

እአአ 2014 ከቦርኖ ግዛት ከ270 በላይ ሴት ተማሪዎችን አፍኖ ከወሰደ በኋላ የበርካቶች መነጋጋሪያ ሆኖ የቆየው ቦኩ ሃራም፤ ከናይጄሪያ በተጨማሪ በቻድ፣ ኒጀር እና ካሜሩን በስፋት ይንቀሳቀሳል።

ከሁለት ወራት በፊትም የቡኩ ሀራማ ታጣቂዎች አሳቻ ቦታ ላይ ጠብቀው 47 የናይጄሪያ እና ወደ 100 የሚጠጉ የቻድ ወታደሮችን መግደላቸው ይታወሳል።

ለዓመታት ናይጄያን እና ጎረቤት አገራትን ሲያስጨንቅ በቆየው ቦኮ ሃራም፤ በሚያደርሳቸው ጥቃቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን፤ ቁጥራቸው በውል የማይወታወቅ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል።